የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች፣ ከዐማራ ክልል ጋራ የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሣባቸው አዋሳኝ አካባቢዎች አንዱ ወደኾነው ፀለምቲ ወረዳ፣ ትላንት ቅዳሜ መመለስ ጀምረዋል።
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ተከታተሉ
Your browser doesn’t support HTML5
ትላንት ወደ ወረዳዋ አራት ቀበሌዎች ተፈናቃዮች መመለሳቸው ሲገለጽ፣ የወረዳዋን ከተማ ማይፀብሪን ጨምሮ የስድስት ቀበሌዎች ተፈናቃዮች ዛሬ እና ነገ ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ ከጦርነቱ በኋላ በዐማራ ክልል መንግሥት የተመሠረተው የጠለምት ወረዳ አስተዳደር የጸጥታ መዋቅር፣ ከሦስት ቀናት በፊት በግዳጅ ሥራ እንዲያቆም መደረጉን፣ የጠለምት ዐማራ ወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አለቃ አለነ አሰጋ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡
ተመላሽ ተፈናቃዮች ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋራ በመኾን፣ የራሳቸውን የጸጥታ መዋቅር እና አስተዳደር ከዘረጉ በኋላ የይገኛል ውዝግቡ በሕዝበ ውሳኔ እንደሚመለስ በፌደራል መንግሥቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ትላንት ቅዳሜ፣ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፊት ወደነበሩበት ፀለምቲ ወረዳ ማይ ዓይኒ ቀበሌ ከተመለሱት ተፈናቃዮች መካከል የኾኑት አቶ ሙላው ዓለማየሁ፣ በእንዳባጉና መጠለያ ለሦስት ዓመታት መቆየታቸውን ለአሜሪካ ድምፅ አውስተዋል፡፡
አቶ ሙላው፣ ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ከመንደራቸው ሰዎች ጋራ ቀኑን በደስታ እያሳለፉት እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
አቶ ጉዕሽ አስገዶም የተባሉ ሌላ ተመላሽ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ ወደ ቀዬአቸው በመመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ “ታጣቂዎቹ እስከ አሁን አልወጡም፤ እንደሰማነውም ትጥቃቸውንም አላወረዱም፡፡ ዛሬ ሌሊት ምን ይደርስብን ይኾን በሚል በስጋት ነው ያደርነው፡፡ ሕዝቡ እንኳን በደኅና መጣችኹ ብሎ በመልካም ነው የተቀበለን፡፡ የሚያሳስበን የታጣቂዎቹ ነገር ነው፡፡” ሲሉ ስጋታቸውንም አጋርተዋል።
ትላንት ቅዳሜ፥ ከማይ ዓይኒ፣ ከማይ ኣንበሳ፣ ከመድኃኔዓለም እና ውሕደት ከተባሉ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ በላይ ተፈናቃዮች እንደተመለሱ ተገልጿል፡፡ በዛሬው ዕለትም፣ የከተማዋን ማይ ፀብሪን ጨምሮ የፀለምቲ ወረዳ ስድስት ቀበሌዎች ተፈናቃዮች እንደሚመለሱ ከተፈናቃዮቹ ሰምተናል፡፡
በጉዳዩ ላይ የጠየቅናቸው የጠለምት ዐማራ ወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አለቃ አለነ አሰጋ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ፣ በዐማራ ክልል መንግሥት ቁጥጥር ሥር በገባው የጠለምት ወረዳ የተመሠረተው አስተዳደር የጸጥታ መዋቅር፣ ከሦስት ቀናት በፊት በግዳጅ ሥራ እንዲያቆም መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በሥራ ላይ የቆየው ፖሊስ እና የጸጥታ መዋቅሩ ወደ ዓዲኣርቃይ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ገልጸው፣ እርሳቸው ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ግን ከአካባቢው አለመልቀቃቸውን፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው የጸጥታ ስጋት መኖሩን ጠቁመው፣ መንግሥትም ይህንኑ ተገንዝቦ፣ ነዋሪው ኅብረተሰብ የራሱን የጸጥታ መዋቅር እንዲዘረጋ ማድረግ ይኖርበታል፤ ብለዋል፡፡
የጠለምት ወረዳ የወሰንና የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመኾናቸው፣ በአካባቢው ላይ ያላቸውን የወሰንና የማንነት ጥያቄ፣ በቦታው ላይ ሳሉ ማቅረባቸውን እንደሚቀጠሉም፣ አለቃ አለነ አሰጋ አክለው አመልክተዋል፡፡
ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፊት የፀለምት ወረዳ እየተባለ በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረው አካባቢው፣ ከጦርነቱ በኋላ የጠለምት ወረዳ ተብሎ በዐማራ ክልል መንግሥት ሥር በተዋቀረ አስተዳደር እየተመራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በፌደራሉ መንግሥት እንዲሁም በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት “አከራካሪ” እየተባሉ ከሚጠሩት የትግራይ እና የዐማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አንዱ በኾነው በዚኹ አካባቢ፣ ተመላሽ ተፈናቃዮች ከነዋሪው ኅብረተሰብ ጋራ በመኾን የጋራ አስተዳደር ከአቋቋሙ በኋላ የይገባኛል ጥያቄው በሕዝበ ውሳኔ ምላሽ እንደሚያገኝ፣ በፌደራል መንግሥቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡