ባለፈው መጋቢት ወር ከቢሯቸው ተወስደው በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዝናቡ አበራ፣ በተለያዩ ሆስፒታሎች የልብ እና ሌሎች ሕመሞች ሕክምና እየተከታተሉ መኾናቸውን፣ ምክትላቸው መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡
በሕመማቸው ምክንያት ዛሬ በነበረው ችሎት ላይ እንዳልተገኙም አረጋግጠዋል፡፡ በችሎቱ ውሎ፣ እርሳቸውን ጨምሮ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ወቅት በቁጥጥር ሥር በዋሉ ዘጠኝ ሰዎች ላይ፣ ፍርድ ቤት ለፖሊስ የሰጠውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመቃወም ጠበቆቻቸው ይግባኝ አቅርበው ክርክር ተደርጓል።
በሌላ በኩል፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ዐውድ ሥር በቁጥጥር ሥር ውለው እስከ አሁን ለፍርድ ያልቀረቡ ሦስት የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎችን ጨምሮ አራት ግለሰቦች፣ በጠበቆቻቸው አማካይነት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ መሥርተዋል፡፡