የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች አመላለሳቸው በመጓተቱ ችግራቸው መባባሱን ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሣባቸው የትግራይ እና የአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን የመመለሱ ሥራ፣ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተፈጸመ ባለመኾኑ ችግራቸው መባባሱን ተፈናቃዮቹ ተናግረዋል፡፡

ከፀለምቲ ወረዳ መፈናቀላቸውን ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ እስከ ግንቦት 30 ቀን እንዲመለሱ ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር አውስተው፣ እስከ አሁን ግን አለመመለሳቸውንና ከክረምቱ ወቅት መዳረስ ጋራ ተያይዞ ችግራቸው ሊባባስ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከፌደራል መንግሥት የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ኾኖም፣ የክልሉ የሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ከላሊ ሓጋዚ፣ በፀለምቲ ወረዳ ከጦርነቱ በኋላ የተመሠረቱ የአስተዳደር እና የጸጥታ መዋቅሮች በፌደራል የጸጥታ ኀይሎች እስከ አሁን እንዲፈርሱ አለመደረጋቸው፣ ለተፈናቃዮቹ በወቅቱ አለመመለስ ምክንያት እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡