በግጭት እየታመሰች በምትገኘው የምሥራቅ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜናዊ ኪቭ ግዛት እየተፈጸመ ያለው ጥቃት እና የዜጎች ሞት እንዲያበቃ፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ፣ ዛሬ እሑድ ተማፅነዋል።
ከትላንት በስቲያ ዐርብ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ከተገደሉና ትላንት ቅዳሜ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ በኋላ፣ በእስላማዊ ዐማፅያን እንደተፈጸሙ በተጠረጠሩ ጥቃቶች የሰዎች ሕይወት ዐልፏል።
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ፣ በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ባሰሙት ንግግር፣ “በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ክፍል በሚፈጸሙት ጥቃቶች እና እልቂቶች አሠቃቂ ዜናዎች መውጣታቸውን ቀጥለዋል፤” ብለዋል።
ብጥብጡን ለማስቆምና የዜጎችን ሕይወት ለመጠበቅ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ፣ አባ ፍራንሲስ፣ በዛሬው እሑድ ሰንበት የሰላም መልዕክታቸው ላይ ጠይቀዋል፡፡
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ፥ በግጭቱ የተገደሉትን “ብዙ ክርስቲያኖች”፥ “ሰማዕታት ናቸው” ሲሉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም፣ በዩክሬን፣ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም ግዛቶች፣ በሱዳን፣ በምያንማር እና “ሰዎች በጦርነት በሚሠቃዩባቸው ስፍራዎች ሁሉ” የሰላም ጥሪን አስተላልፈዋል።