ከትግራይ ክልል ወደ አወዛጋቢዎቹ የራያ አላማጣ እና ራያ ባላ አካባቢዎች ቀደም ሲል ገብተው የቆዩ የታጠቁ ኀይሎች፣ የወረዳዎቹን ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን፣ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ በዐማራ ክልል የተሠየመው የራያ ኣላማጣ ወረዳ ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ፡፡
ከአንድ ወር በላይ ባስቆጠረው የጸጥታ ችግር፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ እንዲሁም ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር 45ሺሕ ማለፉን፣ የወረዳው አስተዳዳሪ ሙሉጌታ አስማማው ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀዋል፡፡
ኀይሎቹ በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ላይም “ሰብአዊ ጥሰት እየፈጸሙ ነው፤” ሲሉ ከሰዋል፡፡ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሃፍቱ ኪሮስ ግን፣ “ከፌደራል ኀይሎች ጋራ በመኾን የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት ከማስፈጸም ውጭ በስም የተጠቀሱት ኃይሎች አካባቢውን ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠሩም፤” ብለዋል፡፡
ተፈጽሟል የተባለውን ሰብአዊ ጥሰትንም “ከእውነት የራቀ” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።