ትግራይ ክልል የጸጥታ ችግር መባባሱን አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት ኹሉን አቀፍ እና አካታች ኾኖ አለመደራጀቱን የተቸው ሣልሳይ ወያነ ትግራይ፣ በዚኹ ክፍተት የክልሉ ጸጥታዊ ችግር ክፉኛ መባባሱን አመለከተ።

የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ አሉላ ኀይሉ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የመዓድን ማውጣት፣ እንዲሁም አስገድዶ መሰወር በክልሉ ተስፋፍቷል።

በጉዳዩ ላይ፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ኾኖም ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በክልሉ ውስጥ ለሚታዩት የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች እና የመሣሪያ ዝውውር ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት እንደሚሠራ በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በሌላ ዜና፣ ከአፋር ክልል ተፈናቅለው በመቐለ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ "መንግሥት ረስቶናል" ሲሉ፣ ቅሬታቸው ለአሜሪካ ድምፅ አሰምተዋል።

የተፈናቃዮቹን ቅሬታ በተመለከተ፣ ከትግራይ እና ከአፋር ክልሎች፣ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት አመራሮች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።