አርሶ አደሮች በመሬት ይዞታቸው ለመበደር የሚያስችላቸው ዐዋጅ ጸደቀ

Your browser doesn’t support HTML5

አርሶ አደሮች፣ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዲያገኙ የሚፈቅደው ዐዋጅ፣ ዛሬ ማክሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል፡፡

ምክር ቤቱ፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሔደው መደበኛ ስብሰባ፣ የአርሶ አደሩን፣ የአርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ፣ አገሪቱ ከደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እድገት ጋራ ለማጣጣም ያስችላል፤ የተባለውን “የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዐዋጅ” ረቂቅ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡

ላለፉት 18 ዓመታት በሥራ ላይ የነበረውን የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዐዋጅ ቁጥር 456/1997 በማሻሻል የተዘጋጀው ዐዲሱ ዐዋጅ፥ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ እና ከፊል አርብቶ አደሩ፣ እንዲሁም ሴቶች እና ድጋፍ የሚሹ ሌሎችም አካላት፣ በመሬት ላይ ያላቸውን መብት የሚያሻሽል እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡

ከማሻሻያዎቹ መካከልም፡- አርሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ፣ በገጠር መሬት ይዞታው ላይ ያለውን የተጠቃሚነት መብት በማረጋገጥ፣ ከፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ብድር እንዲያገኙ ማስቻሉ አንዱ ነው፡፡

በዐዋጁ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችንና ግብዓቶችን በተመለከተ፣ ለምክር ቤቱ ያብራሩት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን ላሌም፣ ይህንኑ አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮች፣ ከባንኮች ብድር ለማግኘት በማስያዣነት የሚሰጡት በመሬቱ ላይ የመጠቀም መብታቸውን እንደኾነ የሚደነግገው ዐዋጁ፣ አንድ የገጠር መሬት ባለይዞታ፣ የመጠቀም መብቱን ሌላ ሰው ከፋይናንስ ተቋማት ለሚበደረው ብድር ዋስትና ማስያዝ እንደሚችልም ይፈቅዳል፡፡

ባለይዞታው ብድሩን መመለስ ባይችል፣ አበዳሪው በዋስትና የያዘውን መሬት መጠቀም እንጂ መሸጥ አይችልም፡፡

አበዳሪው በመሬቱ የሚጠቀምበት የጊዜ ጣሪያ፣ በየክልሎች የሚወሰን ኾኖ፣ ጣሪያው ግን ከ10 ዓመት መብለጥ እንደሌለበት ተመልክቷል፡፡

የገጠር መሬትን ዋስትና አድርጎ ማስያዝን በሚመለከት የሚደነግግ ሕግ እስከ አሁን ባለመኖሩ፣ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት፥ የገጠር መሬት የይዞታ መብትን በመያዝ ብድር የሚሰጡበት አሠራር ለሕጉ መሻሻል በመነሻነት ተጠቅሷል፡፡

ድንጋጌው፣ ከዚኽ ቀደም የብድር እና ቁጠባ ተቋማት የሚሰጡትን ብድር የሚተካ ሳይኾን አማራጭ እንደኾነም ተገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው፣ በቡድን ከብድር እና ቁጠባ ተቋማት ብድር የማግኘት አማራጭም ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡

ዐዲሱ ዐዋጅ፣ የሴቶች እና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ አካላትን በመሬት የመጠቀም መብትን አሻሽሎ አቅርቧል፡፡ ለአብነትም፣ የዐዋጁ አንቀጽ 23፣ “ማንም ወንድ በትዳር ላይ እያለ ሌላ ሴት ካገባ፣ ከራሱ የመሬት ይዞታ ድርሻ ላይ ለሚያገባት ሴት ያካፍላል፤” ይላል፡፡

ከዚህ በፊት፣ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት የተከለከለ ነው፤ በሚል ክልሎች ግራ ሲጋቡበት የነበረውን አሠራር እንደሚቀርፍ የተገለጸው ይኸው የዐዋጁ ድንጋጌ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነሥቶበት አቶ ሰሎሞን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት፣ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች፣ እንዲሁም፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት የገጠር መሬት በነጻ ሊያገኙ የሚችሉባቸውን ዝርዝር ጉዳዮችና በመሬቱ ላይ ስለሚኖራቸው መብትም ዐዋጁ አካቷል፡፡

በአዋጁ አንቀፅ 62፣ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ተግባራት እና ቅጣቶች የተዘረዘሩ ሲኾን፣ ከነዚህም መካከል፣ መሬት መሸጥንና መግዛትን ጨምሮ በገጠር መሬት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ተግባራት፣ እስከ አምስት ዓመት እስር እና የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስከትል የተደነገገው ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም የግል፣ የወል ወይም የመንግሥት ይዞታን በሕገ ወጥ መንገድ የወረረ፣ ጉዳት ያደረሰ፣ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ማንኛውንም ግንባታ የሠራ ወይም እንዲሠራ የፈቀደ፣ ከዕቅድ ውጪ ይዞታውን ጥቅም ላይ ያዋለ፣ ሐሰተኛ የመሬት ይዞታ ማስረጃ ያቀረበ፣ እንደየጥፋቱ መጠን የገንዘብ እና የእስር ቅጣት እንደሚጣልበት ተደንግጓል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰባት ወራት በፊት፣ ኅዳር ወር ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቅ ደረጃ የቀረበው ዐዋጁ፣ ባለፉት ወራት ከትግራይ ክልል በስተቀር አርሶ አደሮችን ጨምሮ ከባለድርሻዎች ጋራ ውይይቶች እንደተደረጉበት ተገልጿል፡፡