በአየር ንብረት ዘጋቢዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ጨምሯል

Your browser doesn’t support HTML5

"ጋዜጠኝነት በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ውስጥ” በሚል መሪ ቃል የተከበረውን የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (UNESCO) ባወጣው ሪፖርት በአካባቢ ለውጥ እና በአየር ንብረት ዙሪያ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እና ማስፈራራት እየጨምረ መሄዱን ገልጾ አስጠንቅቋል። በኢትዮጵያ ከሚዲያ አቅም ማነስ እና ፍላጎት ማጣት ጋር ተያያዞ የአካባቢ ጋዜጠኞች ቁጥር መመናመኑን ባለሞያዎች አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (UNESCO) ዛሬ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ባለፉት 15 ዓመታት ቢያንስ 749 ጋዜጠኞች ወይም የዜና ማሰራጫዎች በአካባቢ ጥበቃ እና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በመዘገባቸው ግድያ፣ አካላዊ ጥቃት፣ ትንኮሳ፣ እስራት እና ሌሎች ሕጋዊ ጥቃቶች እንደተፈፀሙባቸው አስታውቋል። በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ 44 ጋዜጠኞች መገደላቸውንም አስታውቋል።

ዩኔስኮ በ129 አገራት የሚገኙ ከ900 በላይ የአካባቢ ጥበቃ ጋዜጠኞችን አነጋግሮ ባደረገው ጥናት፣ ጋዜጠኞቹ በሚዘግቡት ዘገባ ምክንያት ከተለያዩ አካላት ቀጥተኛ ጥቃት፣ ማስፈራራት እና ጫና እንደሚደረግባቸው አመልክቶ፣ በተለይ ሴት ጋዜጠኞች ከወንዶች ጋዜጠኞች በበለጠ በኢንተርኔት ላይ ለሚፈፀሙ ትንኮሳዎች መጋለጣቸውን አስምሮበታል። ሲሳይ ሳህሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታተመው የሪፖርተር ጋዜጣ ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ ነው።

ዛሬ የሚከበረውን የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን አስመልክቶ፣ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በአወጣው 180 ሀገራትን ያካተተ የዓለም ፕሬስ ነፃነት ዝርዝር መግለጫ፣ ኢትዮጵያ አምና ከነበራት 130ኛ ደረጃ አሽቆልቁላ ወደ 141ኛ ደረጃ ወርዳለች።

በኢትዮጵያም ጋዜጠኝነት ላይ ከተጋረጡ በርካታ ፈተናዎች ጋር ተያይዞ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሳቸው ያሉትን እንደ ድርቅ እና ጎርፍ የመሳሰሉ በርካታ ችግሮች በቦታው ተገኝቶ ለመዘገብ ጋዜጠኞች ፍርሃት እንደሚያድርባቸው ነው ባለሞያዎች ያናገራሉ። የሚዲያው አቅም ማነስም የአካባቢ ጋዜጠኝነት እንዳይበረታታ እና ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዳይዘገብ ማድረጉን ሲሳይ ያስረዳል።

ሲሳይ ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያን፣ ኬንያን እና ሶማሊያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የደረሰውን የድርቅ አደጋ እና መንግስታት ለችግሩ እየሰጡ ያሉትን ምላሽ ዳስሶ ባወጣው ዘገባ ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ሽልማት አግኝቷል። ሆኖም በጋዜጠኝነት በሰራበት ያለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ የሚዘግብ ጋዜጠኛ አለማየቱን ይናገራል።

ሲሳይ ጋዜጠኝነትን ከመቀላልቀሉ ቀደም ብለው በነበሩት ዓመታት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ጋዜጠኞች ማህበር ተቋቁሞ፣ ጋዜጤኞች በአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ዘገባዎችን እንዲሰሩ ያበረታቱ ነበር። በሀገር ውስጥ እና በውጪ የሚዘጋጁ ስልጠናዎችን ያገኙ ጋዜጠኞችም በጉዳዩ ላይ እውቀቱ ኖሯቸው፣ ስለችግሩ ጥልቀት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን ይሰሩ ነበር።

ከነዚህ ጋዜጠኞች አንዱ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ህትመት ሚዲያዎች ላይ ይሰራ የነበረው ውድነህ ዘነበ አንዱ ሲሆን፣ በዛን ወቅት የነበሩ ጋዜጠኞች በብዛት ከሀገር መውጣታቸው ለአካባቢ ጥበቃ ዘገባ መመናመን አስተዋፅኦ አድርጓል ይላል።

የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ አደጋዎችን እያስከተለ ነው። ለምሳሌ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከሰተው ድርቅ በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ሲሆን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ለሞት፣ ለስደት እና ለረሃብ አጋልጧል። በምስራቅ አፍሪካም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ13 ሚሊየን በላይ እንሳት በድርቅ እና በጎርፍ አደጋ ሲሞቱ፣ በመቶ ሺዎች በሚቆጠር ሄክታር ላይ የነበረ ሰብል መውደሙን የኦክስፋም መረጃ ያሳያል። ታዲያ ለምን ሚዲያው ትኩረት ነፈገው? ውድነህ ምላሽ አለው።

ችግሩ የብዙ ነገሮች ድምር ነው የሚለው ሲሳይም፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑም አስተዋፅኦ እንዳለው ያብራራል።

የዓለም ሙቀት መጠን እየጨመረ በሄደ ቁጥር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ተጽእኖዎችም እንዲሁ ተባብሰው መሄዳቸውን ይቀጥላሉ። እነዚህን ችግሮች ህብረተሰቡ አውቆ እንዲዘጋጅ፣ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ የሰዎችን እና የእንስሳትን ህይወት ማዳን የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ተግባር ላይ እንዲውል ግፊት ለማድረግ የሚዲያው ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ሲሳይ ያሰምርበታል።

በየዓመቱ በሚከበረው የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ጋዜጠኞች በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሲሰጣቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ዓለም ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ድንገተኛ ለውጦች እያስተናገደች መሆኑን እና በዚህ ምክንያት በወደፊት ትውልዶች እና ህልውና ላይ ስጋት መፈጠሩን ያመለከተው የመንግስታቱ ድርጅት ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት ህብረተሰቡን በማስተማር ለውጡን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስምሮበታል።