በተከሳሶቹ የወንጀል ድርጊት “ተገድለዋል” የተባሉ ሰዎች፣ በክሱ ላይ በስም እንዲጠቀሱ ብይን ሰጥቶ የነበረው ፍርድ ቤቱ፣ በዛሬው ክርክር ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን፣ ከተከሳሾች ጠበቆች አንዱ ሰሎሞን ገዛኸኝ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
በእነዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ፣ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በዐቃቤ ሕግ የሽብር ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾች፣ ዛሬ ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ችሎት ቀርበዋል፡፡
የዛሬው ችሎት የተቀጠረው፣ ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤት በታዘዘው መሠረት ክሱን አሻሽሎ ማቅረቡን ለመመልከት ነበር፡፡
የዐቃቤ ሕግ ክስ፣ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት የሽብር ወንጀል፣ የ217 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ብዙዎች መጎዳታቸውንና ከፍተኛ ንብረትም መውደሙን ሲያስረዳ፣ በተከሳሽ ጠበቆች ጥያቄ መሠረት፣ ሟቾቹ በስም ተጠቅሰው፣ ሌሎች ጉዳቶችም በዝርዝር ተገልጸው ክሱ እንዲሻሻል፣ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ኅዳር 12 ቀን በይኖ ነበር፡፡
ኾኖም፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ክሱ እንዲሻሻል የተሰጠው ብይን እንዲሻር በደብዳቤ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ለዚኽም በምክንያትነት ያቀረበው፣ እንደ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ የሟቾቹን ስም መጥቀስ “ምስክሮቹን ለጉዳት የሚዳርግ ነው፤” የሚል እንደኾነ፣ ከተከሳሽ ጠበቆች አንዱ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡
ጠበቆች በበኩላቸው፣ ዐቃቤ ሕግ የፍርድ ቤቱን ብያኔ አክብሮ ክሱን የማያሻሽል ከኾነ ክሱ እንዲነሣ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ፣ በጉዳዩ ላይ ትእዛዝ ለመስጠት ለግንቦት 12 ቀን መቅጠሩን፣ ጠበቃ ሰሎሞን ገዛኸኝ አመልክተዋል፡፡
በክስ መዝገቡ ላይ ከተጠቀሱ 51 የሽብር ወንጀል ተከሳሾች መካከል አራት የመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎችን ጨምሮ 23ቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ለሕክምና እንደወጡ ማምለጣቸውን፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ተወካዮች ከዚኽ ቀደም ለፍርድ ቤት ማሳወቃቸውን ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡
ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ የሚገኙ ተከሳሾችን፣ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ውጤቱ ለቀጣዩ ችሎት እንዲቀርብም ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡