ፔፕፋር የግጭት ጫና ባየለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ እንደሚያተኩር አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

በዩናይትድ ስቴትስ 43ኛ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋከር ቡሽ የተጀመረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤድስ አጣዳፊ ድጋፍ መርኃ ግብር በምኅጻሩ ፔፕፋር፣ የኢትዮጵያ ተጠባባቂ አስተባባሪ ቤንጃሚን ካስዳን ዛሬ ረቡዕ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ በአገሪቱ ያሉት ግጭቶች፣ በሽታው እንዲስፋፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ለአብነትም፣ በትግራይ ክልል በተደረገ የዳሰሳ ጥናት፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በሽታው በክልሉ በስፋት መዛመቱን አሳይቷል፤ ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤድስ አጣዳፊ ድጋፍ መርኃ ግብር (ፔፕፍር) ፣በኢትዮጵያ በሚያከናውነው ሥራ፣ በግጭት ተጽእኖ ውስጥ ለሚገኙ አካባቢዎች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቋል።

የመርሐ ግብሩ ተጠባባቂ አስተባባሪ ቤንጃሚን ካስዳን ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መኾኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ክልልን መነሻ ባደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት፣ በክልሉ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ከአገራዊው አማካይ ምጣኔ በላይ 15 ከመቶ መድረሱን አስተባባሪው በማሳያነት ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚሠሩ አንድ ባለሞያ ደግሞ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚታዩት ግጭቶች በተጨማሪ፣ የኮንዶም እጥረት እና ሌሎችም ችግሮች በሽታውን በመከላከል ሥራ ላይ ተጽእኖ ማሳደራቸውን አመልክተዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ከሀብት ውስንነት ጋራ የተያያዘ የኮንዶም እና የሌሎችም ግብአቶች እጥረት መኖሩን አስታውቋል፡፡