ሴኔቱ ቁልፍ የውጭ መረጃ ክትትል ህግን እንደገና አራዘመ

  • ቪኦኤ ዜና
የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት

የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት የአሜሪካን ደህንነት ለማስጠበቅ በሌላ ሀገር የሚገኙ የውጭ ዜጎችን ለመመረጅና ለመከታተል የሚያስችለውን የውጪ መረጃ ክትትል ህግ ለሁለት ዓመት እንዲራዘም ዛሬ ቅዳሜ ወሰነ፡፡

ምክር ቤቱ ህጉን ያሳለፈው 60 ለ34 በሆነ ድምጽ ሌሊቱን ባሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡

ዛሬ ቅዳሜ አጥቢያ እኩለ ሌሌት ካለፈ በኋላ ተግባራዊነቱ አብቅቶ የነበረውና እንዲቀጥል የተወሰነው ይህ ህግ፣ የውጪ መረጃ ክትትል ህግ ክፍል 702 ተብሎ ይታወቃል፡፡

በፕሬዚዳንት ባይደን ከተፈረመ በኋላ የሚጸድቀው ህግ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ካልሆኑ የውጭ ተቋማትና ግለሰቦች መረጃዎችን ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲያሰባስቡ ለአሜሪካ መረጃ ድርጅቶች ሥልጣን ይሰጣል፡፡

ህጉ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ የመረጃ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ)” አሜሪካውያንን እንዲሰልል በር ይከፍታል” የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ቢነሳበትም ኤፍ ቢ አይ የአሜሪካውያንን መረጃ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማግኘት መብትን ለመገደብ የታቀዱ ስድስት ማሻሻያዎች በመጨረሻው ሕግ ውስጥ አልተካተቱም።

ተቺዎች የስለላው አሰራር አሜሪካውያንን የሚያካትቱ ግንኙነቶችና መረጃዎችንም ሊሰበስብ የሚችልበት ክፍተት ይኖራል ሲሉ ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል፡፡

በህግ ተደግፎ የሚተገበረው መርሃግብር የሽብር ጥቃቶች፣ የሳይበር አደጋዎችን፣ከውጭ የሚሰነዘሩ ሌሎች የደህንነት ስጋቶችን ለመካለከል ያስችላል ተብሏል፡፡

እኤአ በ2022 የአልቃይዳ መሪ አይመን አል ዛዋህሪን የመሳሰሉ ግድያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሥራ ላይ መዋሉም ተገልጿል፡፡