የትረምፕ ክስ ከሚታይበት ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ራሱን ያቃጠለው ግለሰብ ህይወቱ አለፈ

  • ቪኦኤ ዜና
ፖሊሶች በኒዮርክ ከተማ ራሱን በእሳት ያቃጠለው ግለሰብ ድርጊቱን የፈጸመበትን ቦታ ትላንት መርምረዋል እኤአ ኤፕሪል 19

ፖሊሶች በኒዮርክ ከተማ ራሱን በእሳት ያቃጠለው ግለሰብ ድርጊቱን የፈጸመበትን ቦታ ትላንት መርምረዋል እኤአ ኤፕሪል 19

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ የተከሰሱበትን ጉዳይ ለመመልከት በኒዮርክ ከተሰየመው ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ትላንት ዓርብ ራሱን ያቃጠለው ግለሰብ ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የኒውዮርክ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዛሬ ቅዳሜ ማለዳ ለአሶሴይትድ ፕሬስ እንደተናገረው፣ በአካባቢው የሚገኝ ሆስፒታል ሠራተኞች ግለሰቡ መሞቱን አስታውቀዋል።

ሟች ትላንት ከሰዓት ወደ 1፡30 አካባቢ ኮሌክት ፓርክ በሚባለው ኩሬ አካባቢ፣ የተጎነጎኑ ሴራዎች መኖራቸውን የሚናገሩ በራሪ ወረቀቶችን እያሳየ ወዲያና ወዲህ ሲንጎራደድ ቆይቶ ከመቅጽበት ራሱን በእሳት ማቀጣጠሉን ባለሥልጣናትና የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ ሲፈጸም ብዙ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ አባላት በአቅራቢያው ነበሩ ፡፡ አንዳንድ ፖሊሶችና በቦታው የነበሩ ሰዎችም ግለሰቡን ለመርዳት በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ወስደውታል፡፡

ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ግለሰቡ ከፍሎሪዳ ወደ ኒውዮርክ ተጉዞ የመጣው ባለፉት ጥቂት ቀናት ነው ብሏል፡፡

ባለፈው ሰኞ በዳኞች ምርጫ በጀመረው የትረምፕ የፍርድ ሂደት፣ የተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች እና ተመልካቾች መሰብሰቢያ ሁኖ ወደ ቆየው ፓርክ ውስጥ በመግባትም የፈጸመውም ሆነ የተላለፈው ምንም ዓይነት የደህንነት ደንቦችን የሉም ሲል ፖሊስ አስታውቋል።