ፖሊስ ከበቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋራ በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

በምሥራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ጠዋት ተገድለው ከተገኙት የኦነግ ከፍተኛ አመራር አቶ ቤቴ ዑርጌሳ ኅልፈት ጋራ በተያያዘ፣ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገለጸ።

መንግሥታዊ ብዙኀን መገናኛዎች፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መመሪያ አዛዥን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት፣ እስከ አሁን ተደረገ በተባለው ክትትል 13 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በዚኹ ጉዳይ ላይ፣ የአሜሪካ ድምፅ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ እና ከመቂ ከተማ ፖሊስ ኃላፊዎች ለማጣራት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

በሌላ ዜና፣ ሁለት የአቶ በቴ ቤተሰብ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁና የቅርብ ዘመድ ነኝ ያሉ ምንጭ ፤“ትላንት ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ፣ አንድ የበቴ ዑርጌሳ ወንድም እና አንድ እህቱ በፖሊስ ተይዘው ነበር። የበቴ እህት ፣ስምቦ ዑርጌሳ አንድ ሰዓት አካባቢ ተለቃለች፤። ወንድሙ ግን ፈጣን መንገድ በሚባለውና ገብርኤል አካባቢ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ተወስዷል።” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።