ኬንያ ከቱሪዝም ከኮቪድ በፊት የተሻለ ገቢ አገኘች

ፎቶ ፋይል (ኤፒ ጥር 11 2023)

ኬንያ፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2023፣ ከቱሪዝም ያገኘችው ገቢ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፊት ከነበረውም የተሻለ እንደሆነ የሃገሪቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል። ገቢው በሶስት እጥፍ በሚባል መጠን ማደጉም ተነግሯል።

ኬንያ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የምትስብ ሃገር ነች፡፡ የዱር አራዊቶቿና በሕንድ ውቅያኖስ የሚገኙት የባሕር ዳርቻ መዝናኛዎች ዋናው የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ትኩረት ናቸው። ኤኤፍፒ ተመልክቼዋለሁ ያለውን የሚኒስቴሩን ሪፖርት ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ከቱሪዝም የተገኘው ገቢ በ31.5 በመቶ በማደግ፣ 2.7 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል። ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፊት የነበረው የቱሪዝም ገቢ 2.24 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

ነገር ግን እያንዳንዱ ቱሪስት በጉብኝት ወቅት የሚያጠፋው የገንዘብ መጠን ከ2022 አንፃር ቀንሷል ተብሏል። ይህም በከፊል ምክንያቱ የኬንያ ሺሊንግ ከዋና መገበያያ ገንዘቦች አንፃር አቅሙ እየተዳከመ በመምጣቱ ነው ተብሏል።

በ2023 ኬንያ 1.95 ሚሊዮን ቱሪስቶችን እንዳስተናገደችም ታውቋል። ሃገሪቱን ከሚጎበኙ የውጪ ዜጎች ውስጥ አሜሪካውያን ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ። ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 265ሺሕ 310 አሜሪካውያን ኬንያን ጎብኝተዋል። ቀጣዩን ቁጥር የያዙት ከጎረቤት ዩጋንዳ የሚመጡ ቱሪስቶች ሲሆኑ፣ ባለፈው ዓመት 201ሺሕ 623 ዩጋንዳውያን ጎረቤት ኬንያን ጎብኝተዋል።