ንግድ ባንክ ከተወሰደበት ገንዘብ እስከ አሁን 80 በመቶውን እንዳስመለሰ ተገለጸ

Your browser doesn’t support HTML5

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከ10 ቀናት በፊት ባጋጠመው የሥርዐት ችግር ከተወሰደበት ገንዘብ ውስጥ እስከ አሁን 80 ከመቶውን ማስመለሱን፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ተናገሩ፡፡

በጉዳዩ ላይ ብሔራዊ ባንክ ሙሉ ምርመራ እያካሔደ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ማሞ፣ ግኝቱን የሚመለከት ሪፖርትም ከሳምንት በኋላ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ባጋጠመው የሥርዓት ችግር ምክኒያት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተወሰደበት ያስታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ፣ እስከ አሁን 622 ሚሊዮን ብር ማስመለሱን ዛሬ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

በአንድ የዲጂታል አገልግሎት መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ፣ በአሁኑ ወቅት ንግድ ባንክን ጨምሮ በርካታ ተቋማት፣ አገልግሎታቸውን በዲጂታል አሠራር እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ይህን ሥርዓት የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት በቅርቡ ይቋቋማል፤ ብለዋል።