በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ ወረዳዎች የተቀሰቀሰው ማንነት ተኮር ግጭት መፍትሔ ሳያገኝ አንድ ሳምንት እንዳለፈው፣ የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው የተጎራባቾቹ የኤፍራታ ግድም እና የጅሌ ጥሙጋ ወረዳዎች ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡
ግጭቱ አድማሱን አስፍቶ ትላንት ማክሰኞ እና በዛሬው ዕለት፣ በአጣዬ ከተማ ውስጥ ከባድ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በተኩስ ልውውጡ ከሁለቱም ወገኖች የበርካታ ሰላማውያን ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ንብረት መዘረፋን፣ ቤቶች እና ሰብሎች መቃጠላቸውን አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል፡፡
ለዚኹ ጥቃት ከሰሜን ሸዋ ዞን በኩል፣ መንግሥት፥ ኦነግ ሸኔ የሚለውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አባገዳ ደግሞ፣ ውጊያው ላይ የተሳተፉት የኦሮሞ አርሶ አደሮች ናቸው፤ ይላሉ፡፡
ግጭቱ የዛሬ ዓመት ገደማ እንደተቀሰቀሰ ያወሱት፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ነዋሪ፣ በየጊዜው አድማሱን አስፍቶ ለሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ምክንያት እየኾነ እንዳለ አመልክተዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የኤፍራታ ግድም ወረዳ ነዋሪው ደግሞ፣ ችግሩ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት እንደሚጠይቅ አመልክተው፣ “ጥፋት ካለ በሕግ መጠየቅ እንጂ በጅምላ ማውደም ተገቢ አይደለም፤” ይላሉ፡፡
የአጣዬ ከተማ ከንቲባ ተመስገን ተስፋ፣ ከተማዋ እና ነዋሪዋ ለጥቃት መጋለጣቸውን አረጋግጠው፣ መንግሥት እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አመራሮችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ
Your browser doesn’t support HTML5