መንግሥት ጋዜጠኛ ሙሄዲን መሐመድን ፈጥኖ እንዲፈታ ሲፒጄ ጠየቀ

  • ቆንጂት ታየ

በሶማሊኛ ቋንቋ የሚተላለፈው ‘ካልሳን ቲቪ’ የቀድሞ ዘጋቢ እና ከአንድ ወር በፊት በሶማሌ ክልል ውስጥ የታሰረው ሙሄዲን መሐመድ። ፎቶ - ሲፒጄ

በሶማሊኛ ቋንቋ የሚተላለፈው ‘ካልሳን ቲቪ’ የቀድሞ ዘጋቢ እና ከአንድ ወር በፊት በሶማሌ ክልል ውስጥ የታሰረው ሙሄዲን መሐመድ፣ ያለቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቅ፣ ሲፒጄ ጠየቀ።

ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ ማሰርም መቆም እንደሚገባው፣ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅቱ አሳስቧል፡፡

መቀመጫውን ለንደን ላደረገው ‘ካልሳን ቲቪ’ የሶማልኛ ቋንቋ ብዙኀን መገናኛ ሲሠራ የነበረው ሙሄዲን መሐመድ የታሰረው፣ “በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል” ከተባለው የተሳሳተ ጽሑፍ ጋራ በተያያዘ ነበር፡፡

ሙሄዲን፣ ጅግጅጋ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከአንድ ወር በፊት ተወስዶ መታሰሩን፣ የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማኅበርን ጠቅሶ ሲፒጄ፣ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የሙሄዲንን መታሰር፣ አዲስ ስታንዳርድ ከተባለው ብዙኀን መገናኛ ገጽ ላይ ማግኘቱን የጠቀሰው የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋቹ ሲፒጄ፣ የክስ ዶሴውንም እንደተመለከተው አስታውቋል።

የክልሉ ጋዜጠኞች ማኅበር ሊቀ መንበር አብዱረዛቅ ሐሰን ነግረውኛል ያለውን መረጃ በመግለጫው ያካተተው ሲፒጄ፣ በሙሄዲን ላይ፣ የሐሰት ዜና እና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት ወንጀል ክስ እንደቀረበበት ገልጿል።

ሙሄዲን፣ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በቀረበበት በዚኹ ክስ ጥፋተኛ ከተባለ፣ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ድርጅቱ ጠቁሟል።

የጋዜጠኛው “ብቸኛ ወንጀል”፣ በፌስቡክ ገጹ የፖለቲካ ልሂቃንን መተቸቱ እንደኾነ የጠቆሙት የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ፣ “የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት ጋዜጠኞችን በመክሰስ የሕዝብ ሀብት ማባከን የለባቸውም፤” ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ መንግሥትን የሚተቹ ጋዜጠኞችን ማሰር ማቆም እንዳለበት ሙቶኪ አክለው አሳስበዋል።

ሲፒጄ፣ የክልሉን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መጠየቁን ገልጾ፣ “እንደ ዜጋ ሕገ መንግሥታዊ እና ሰብአዊ መብቶች ያላቸው አቶ ሙሄዲን በመታሰራቸው በጥቅል እናዝናለን፤ ነገር ግን እንደ ዜጋ በሚሠሩት ሥራ መጠየቅ አይችሉም ማለት አይደለም፤” የሚል ምላሽ ማግኘቱን በመግለጫው ጠቅሷል።

የሶማሌ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዓሊ አብዲጃባር አስተያየታቸውን እንዲሰጡት ሲፒጄ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ለጊዜው ምላሽ እንዳልሰጡት አክሏል።

ሲፒጄ፣ እ.አ.አ. ታኅሣሥ 1 ቀን 2023 ባወጣው፣ በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ሪፖርቱ፣ ስምንት ጋዜጠኞች የታሰሩባት ኢትዮጵያ፣ በታሰሩ ጋዜጠኞች ብዛት ከሰሃራ በታች ካሉት የአፍሪካ ሀገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የተጣለውንና ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተከትሎ፣ አራት ጋዜጠኞች ክስ ሳይመሠረትባቸውና ያለፍርድ ሒደት መታሰራቸውን ሲፒጄ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡