በደላንታ ወረዳ ዋሻ የተናደባቸውን የኦፓል አምራቾች ለመታደግ ጥረቱ ቀጥሏል

ጉግል ካርታ ደላንታ 2016

ጉግል ካርታ ደላንታ 2016

በክልሉ ደቡብ ወሎ ዞን በኦፓል ማዕድን ሀብቷ በምትታወቀው ደላንታ ወረዳ በባህላዊ መንገድ የኦፓል ማዕድን የሚያመርቱ ወጣቶች፣ ኀሙስ ጥር 30 /2016 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ገደማ ዋሻ ውስጥ በቁፋሮ ላይ እያሉ በግዙፍ ናዳ በመያዛቸው ሕይወታቸውን ለመታደግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የወረዳው አስተዳደር ገለጸ፡፡

750 ሜትር ርዝመት እንዳለው በተገለጸው በዚሁ ዋሻ ውስጥ በተቆፈረ 25 ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ በናዳው የተያዙ ሰዎችን ብዛት በውል ለማወቅ ባይቻልም፣ ከዐሥር በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የወረዳው ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አብዮት ጌታሁን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ መንግሥታዊ መዋቅሩ እና ቤተሰቦቻቸው፣ ማዕድን አውጪዎቹን ለመታደግ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በኦፓል የከበረ ማዕድን ንግድ ላይ የተሰማሩትና በናዳው ከተያዙት መካከል፣ የጓደኛቸው መለሰ መብሬ ቤተሰቦች እንደሚገኙባቸው የገለጹት ወንድወሰን ታደሰ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ፣ በዋሻው ውስጥ ሳሉ በናዳው ውስጥ የቀሩ ሰዎች ከ20 በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በናዳው ከተያዙት አብዛኞቹ ወጣቶች እንደሆኑና ሥራውን ከጀመሩ ከሰባት ዓመት በላይ እንደሆናቸው፣ አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡ ብዙዎቹም ቤተሰባቸውን የሚያስተዳደሩት፣ ለሕይወታቸው በሚያሰጋ ቁፋሮ ያወጡትን ኦፓል፣ ከልፋታቸው ጋራ በማይመጣጠን ዋጋ እየሸጡ ነው፤ ብለዋል፡፡

ደስታው ዓሊ የተባሉ የወገል ጤና ከተማ ነዋሪ፣ በዋሻ ውስጥ በናዳ የተያዙ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ባላቸው መሣሪያ እየቆፈሩ የነፍስ አድን ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የደላንታ ወረዳ ማዕድን ጽ/ቤት ኃላፊ ተስፋው ሰማው፣ በክልላዊ መንግሥቱ ለሚደገፈው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት፣ የሕይወት አድን ጥረቱ ለዋሻው መግቢያ ቅርበት ባለው የውስጠኛው ክፍል ላይ አተኩሮ እየተካሔደ ነው፡፡

እስከ አሁን በሰው ኃይል ከ50 ሜትር በላይ መቆፈሩን ጠቁመው፣ ቦታው አመቺ ባይሆንም በተለያዩ ማሽኖች በመታገዝ ቁፋሮውን ለማፋጠን ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ናዳው በተከሠተበት አካባቢ ብቻ፣ ከ400 እስከ 500 ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው በኦፓል ማምረት ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ከወረዳው አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የደላንታ ወረዳ ከ2004 ዓ.ም. አንሥቶ በኦፓል ማዕድን ምርቷ ትታወቃለች፡፡ ወረዳዋ ካሏት 32 ቀበሌዎች ውስጥ በ30ዎቹ ውስጥ የኦፓል ማዕድን ሀብት እንዳላት ቢነገርም፣ አመራረቱም ሆነ አካባቢው ገደላማ በመሆኑ፣ ዘመናዊ አሠራርን መከተል ካልተቻለ ወደፊትም ተመሳሳይ አደጋዎች ሊከሠቱ እንደሚችሉ አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡