በሴኔጋል የፀጥታ ኃይሎች ከሰልፈኞች ጋር ተጋጩ

ተቃዋሚዎች በዳካር ከተማ ሰልፍ በማድረግ ላይ (ፎቶ ኤፒ 02/10/24)

ተቃዋሚዎች በዳካር ከተማ ሰልፍ በማድረግ ላይ (ፎቶ ኤፒ 02/10/24)

በሴኔጋል መዲና ዳካር ተቃዋሚዎች እና የጸጥታ ኃይሎች ትናንት መጋጨታቸው ተዘግቧል። ሰልፈኞቹ የወጡት መንግስት ምርጫውን ማራዘሙን በመቃወም ነበር። ትናንት ዓርብ በጥይት ሆዱ ላይ የተመታ የ23 ዓመት ወጣት ዛሬ መሞቱ ሲታወቅ፣ በሰሜን የአገሪቱ ክፍልም አንድ ተማሪ ትናንት መገደሉን የኤኤፍፒ ዘገባ አመክቷል።

ሰልፈኞቹ ድንጋይ ሲወረውሩ፣ የጸጥታ ኃይሎች በአጸፋው አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅመዋል።

ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊካሄድ የታቀድውን ምርጫ የአገሪቱ ፓርላማ ባለፈው ሰኞ ባደረገው ስብሰባ በአስር ወራት እንዲራዘም ወስኗል።ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕዝቡ የፓርላማውን ውሳኔ በሰልፍ እንዲያወግዝ ጠይቀዋል። ውሳኔው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን አሳስቧል ተብሏል።

የፓርላማው ውሳኔ የወቅቱ ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ በስልጣን እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው።

በመፈንቅለ መንግስት በታበጠው ቀጠና፣ ሴኔጋል የመረጋጋትና ዲሞክራሲ ምልክት ተደርጋ ብትታይም፣ የሰሞኑ ቀውስ ግን ጥርጣሬን ጭሯል።