የኤርትራ ወታደሮች፣ ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ጋራ አዋሳኝ በሆኑ የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችን እያፈኑና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶችን እየዘረፉ እንደሆነ፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ ተመለከትሁት ያለውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ጤና ቡድን አባላት፣ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ላይ ባደረጉት ግምገማ ላይ ተመሥርቶ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ሪፖርቱ፣ በኤርትራ ኃይሎች የተፈጸሙ በርካታ አፈናዎችንና የከብት ዝርፊያዎችን መመዝገቡን፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ ገልጿል። የዜና ተቋሙ ሪፖርቱን ያገኘው፣ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ ከጠየቀ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣን እንደሆነም አመልክቷል።
የኤርትራ ኃይሎች “የሰዎች ጠለፋ እና የከብት ዝርፊያ ፈጽመዋል” መባሉን ተከትሎ፣ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በሰጡት ምላሽ፣ “ሐሰት ነው” ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል።
የጤና ቡድኑ ሪፖርት፣ ጥር 13 ቀን ተፈጸመ ባለው አንድ ክሥተት፣ ስምንት እረኞች ከአህዮቻቸው እና ግመሎቻቸው ጋራ ታፍነው እንደተወሰዱ አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ ኅዳር 26 ቀን ስድስት ሰዎች ከ56 የቤት እንስሳት ጋራ እንደታፈኑና ኅዳር 25 ቀን ደግሞ የኤርትራ ኃይሎች 100 እንስሳትን እንደሰረቁም ጠቅሷል።
ሰነዱ አክሎ፣ በድንበር ላይ የሚገኙ ሁለቱ ወረዳዎች “ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል” በኤርትራ ጦር ጥበቃ እንደሚደረግባቸው ጠቅሶ፣ በዚህ ምክንያት በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው መሬታቸውን ማረስ እንደማይችሉ ገልጿል። በሚበዙት የወረዳዎቹ አካባቢዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እንደማይገኙና ለሕዝቡም ጥበቃ እንደማያደርጉ ተመልክቷል።
በተጨማሪም፣ የጤና ቡድኑ ያወጣው ሪፖርት፣ በድርቅ የተጠቁና ለሰብአዊ ርዳታዎች አሰጣጥ በጣም አስቸጋሪ እንደኾኑ በጠቀሳቸው ሺምብሊና እና አዳሜይቲ በተባሉ መንደሮች ውስጥ፣ ከረኀብ ጉዳት የተነሣ ቢያንስ 50 ሰዎች እንደሞቱ መመዝግቡን ዘገባው ጠቅሷል።
ባለፉት ሳምንታት፣ ከድርቅ እና ከርዳታ መቋረጥ ጋራ በተገናኙ ምክንያቶች፣ በክልሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረኀብ ምክንያት ሳይሞቱ እንደማይቀር የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የትግራይ ባለሥልጣናትም፣ ሁኔታው “በክልሉ ከባድ ረኀብ ሊያስከትል እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው፤” ብሏል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ኃይሎች እና የክልሉ ታጣቂ ኀይሎች ለሁለት ዓመታት ባካሔዱት ውጊያ፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁልፍ አጋር ነበረች፡፡ የኤርትራ ወታደሮችም፣ በዜጎች ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸምንና የወሲብ ባርነትን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል፤ የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።
ጦርነቱ በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በተፈረመው የሰላም ስምምነት ሲጠናቀቅ፣ የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ የተጠየቀ ቢሆንም፣ የስምምነቱ አካል ያልሆነችው ኤርትራ፣ አሁንም ከኢትዮጵያ ጋራ በሚያዋስነው ድንበር ላይ በርካታ አካባቢዎችን ይዛ እንደምትገኝ ተዘግቧል።
የተኩስ ማቆም ስምምነቱ አንደኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የኤርትራ ኃይሎች እንዲወጡ በድጋሚ የጠየቁ ሲሆን፣ በትግራይ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት “ተጨማሪ ተግባራት ያስፈልጋሉ፤” ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ ደም አፋሳሹን ጦርነት ቢያስቆምም፣ በአፈጻጸሙ መጓተት የተነሣ በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ወንጀሎች የሚጠበቀው የሽግግር ፍትሕ እንደዘገየና በመቶዎች እና በሺሕዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሒደቱም ገና አለመጀመሩን፣ የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል።
ከትግራይ ኀይሎች ጋራ የተካሔደው ጦርነት ቢያቆምም፣ በጎረቤት በሚገኘው የአማራ ክልል በተስፋፋው ግጭት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከክልሉ ታጣቂዎች ጋራ እየተዋጋ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሔደው ስብሰባም፣ ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ በክልሉ ተጥሎ የቆየውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሟል።