ደሳለኝ ጫኔ ታሰሩ

Your browser doesn’t support HTML5

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ፓርቲን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ትላንት፣ ረቡዕ፣ ጥር 22 / 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ በፖሊስ ተወስደው መታሰራቸውን አንድ የቤተሰባቸው አባል ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስና መለዮ ያጠለቁ ሁለት ሰዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የታጠቁ ሁለት ሲቪል ለባሾች “በሕግ ይፈለጋሉ” ብለው ከመኖሪያ ቤታቸው እንደወሰዷቸው፤ “ለደኅንነቴ እሠጋለሁ” በሚል ማንነታቸውን እንዳንገልፅ የጠየቁን አንድ የዶ/ር ደሳለኝ ቤተሰብ አባል ገልፀዋል።

የፖሊስ ባልደረቦቹና የፀጥታ ሠራተኞቹ ዛሬ ኀሙስ፤ ጠዋት ዶ/ር ደሳለኝን ይዘው መመለሳቸውንና ቤታቸውን ፈትሸው ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስና ሰነዶችን፣ እንዲሁም እራሣቸውን አቶ ደሳለኝንም ይዘው መሄዳቸውን እኒሁ ዘመድ አመልክተዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማረፊያ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል። የዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ጠበቃ አቶ ሰሎሞን ገዛኸኝ ጠበቆች ደንበኛቸውን ማግኘት የሚችሉት ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ መሆኑን ጠቅሰው ነገ፤ ዓርብ ደንበኛቸው ታስረው ወደሚገኙበት እንደሚሄዱ ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሠሩ ሌሎች ደንበኞቻቸውን ማግኘት እንዳልተፈቀደላቸው አቶ ሰሎሞን አስታውሰው ዶ/ር ደሳለኝ የተያዙት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጭ በሆነ ምክንያት ከሆነ ሊያገኟቸው እንደሚችሉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ትናንት ረቡዕ ምሽት ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መታሰራቸውን አንድ የቤተሰባቸው አባል ገለፁ።