ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደ ሥነ ስርዓት ላይ አንድ ሺሕ ጥንዶች በትዳር ተጣምረው በጋራ ሰርጋቸውን አከናውነዋል።
ያሜንት ኃ/የተ/የግ/ ማኅበር የተሰኘ ድርጅት ከባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚሁ የጋራ ሠርግ ላይ፣ ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ አዲስ ሙሽሮች ተካፋይ ሆነዋል።
በባህላዊ አልባሳት ያጌጡት ጥንዶች፣ ሥነ ስርዓቱ ወደተካሄደበት የሚሊኒየም አዳራሽ ሲያመሩ፣ እንደመጡበት ባህል ሲዘፍኑ እና ሲጨፍሩ መስተዋላቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
አዘጋጆቹ ከአሥር ዓመታት በፊትም 500 ጥንዶችን በአንድ ላይ ያጋቡ ሲሆን፣ በኮሮና ወረርሽኝ እና በሌሎችም ምክንያት ተቋርጦ መሰንበቱ ታውቋል።
ከጋምቤላ ክልል የመጡትና ሁለቱም የ21 ዓመት ወጣቶች የሆኑት ያዕቆብ ተስፋዬ እና ልደት ታገል፣ ከሌሎች አካባቢና ባህል የመጡ ጥንዶችን ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረው፣ ለሰርግ የሚሆን በቂ በጀት ስላልነበራቸው መልካም አጋጣሚው እንደነበር ተናግረዋል።