“በአንድ ሳምንት ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች ከሱዳን ኢትዮጵያ ገብተዋል” ዩኤንኤችሲአር

Your browser doesn’t support HTML5

በሱዳን ጦርነት ምክንያት፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ 41 ሺህ በላይ ሰዎች ከሱዳን ሸሽተው ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር /UNHCR/ አስታወቀ፡፡ የተቋሙ የኢትዮጵያ ቢሮ ረዳት ተወካይ አልፍሬድ ካኑ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ከመስከረም እስከ ህዳር በነበሩት ጊዜያት፣ የሱዳኑን ጦርነት ሸሽተው ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ቀንሶ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት ግን በሦስት እጥፍ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ ስ

በአማራ ክልል ለአዲሶቹ ስደተኞች ማረፊያ የሚሆን አዲስ የመጠለያ ጣቢያ እየተቋቋመ እንዳለም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ጦርነቱ ይበልጡን ከተዛመተ፣ እስከ 100 ሺህ ሰዎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ እንደሚችሉም እንገምታለን” ብለዋል፡፡

ከስምንት ወራት በፊት የተቀሰቀሰውን የሱዳኑን ጦርነት ሸሽተው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በመተማ እና በኩርሙክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ እንደነበረ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር /UNHCR/ አስታውሶ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ከመስከረም እስከ ህዳር ድረስ በነበሩት ጊዜያት እየቀነሰ መጥቶ እንደነበረም፣ የተቋሙ የኢትዮጵያ ቢሮ ረዳት ተወካይ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው የፈረንጆቹ 2023 ዓመተ ምሕረት መጨረሻ ላይ ጦርነቱ ወደ ሌሎች የሱዳን አካባቢዎች፣ በተለይም በማዕከላዊ ሱዳን በምትገኘው የጀዚራ ግዛት መስፋፋት ሲጀምር፣ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ብዛት በሦስት እጥፍ መጨመሩን ረዳት ተወካዩ አብራርተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ በግጭቱ መስፋፋት ምክንያት ሊኖር የሚችለውን ከፍተኛ የስደተኞች ፍሰት ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያ ቢሮው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ኅላፊው ገልፀዋል፡፡ ለአዳዲሶቹ ስደተኞች፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብአዊ እርዳታዎችን እየሰጠ እንደሚገኝና፣ ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶችም አስፈላጊ እርዳታ እንደሚያደርጉ ኃላፊው ጨምረው አውስተዋል፡፡

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ጦርነቱን እንዲያቆሙ፣ በዓለምአቀፍ ድንጋጌዎች መሰረት የንፁሃንን ደህንነት እንዲጠብቁ እና በጦርነቱ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች የነፍስ አድን እርዳታ እንዲደርሳቸው እንዲያደርጉ /UNHCR/ ተማፅኗል፡፡

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያድምጡ፡፡