ኢትዮጵያ ዕዳዋን ለምን አልከፈለችም?

Your browser doesn’t support HTML5

ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎች የሚጠበቅባትን ክፍያ በዚህ ወር ያልከፈለችው “አቅም ስለሌላት ሳይሆን ከሌሎች አበዳሪዎች ጋር እየተደረገ ያለውን የብድር እፎይታ ድርድር እንድይጎዳው ነው” ሲሉ የሃገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ደ’ኤታ እዮብ ተካልኝ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ረዳት ፕሮፌሰር ሰውአለ አባተ በበኩላቸው ሁኔታው ሃገሪቱ በአበዳሪዎች እንዳትታመን የወለድ መጠንም እንዲያሻቅብባት ሊያደርግ እንደሚችል አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ላለባት ዕዳ ለዓለምአቀፍ አበዳሪዎቿ ታኅሣስ 16 መክፈል ይጠበቅባት የነበረውን የወለድ ክፍያ ባለመፈፀሟ ዕዳዋ “ሊከፈል የማይችል” ወይም “ያልፈከፈለ” ወይም “የዘገየ ክፍያ” ዶሴ ውስጥ መግባቱ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት፣ በ2007 ዓ.ም. እንደ ፋይናንስ ምንጭና መበደሪያ ይሆናት ዘንድ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ሸጣ በየዓመቱ ከ62 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወለድ ስትከፍል ቆይታለች።

ይሁንና በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከፈለውን የዚህ ወቅት 33 ሚሊየን ዶላር የተሰጣትን የ2 ሣምንት የጊዜ ገደብ ጨምሮ በወቅቱ መክፈል ሳትችል ቀርታለች።

የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰውአለ አባተ “ኢትዮጵያ የብድር ወለድን በጊዜ ገደቡ መክፈል ሳትችል የቀረችበት አቅሟ በዚህ ደረጃ ያሽቆለቆለበት ጊዜ አልነበረም” ይላሉ።

በዚህ ምንክያት “ኢትዮጵያ ከውጭ አበዳሪዎች የምታገኛቸው የፋይናንስ ምንጮች እየቀነሱ መምጣታቸው አይቀርም” የሚሉት ዶ/ር ሰውአለ የዋጋ ንረትን ጨምሮ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኑሮ ላይ ጫና እንደሚያበረታ አስጠንቅቀዋል።

ይህኛው ብድር ድርድር እየተደረገባቸው ካሉ ብድሮች በዓይነቱ የተለየ እንደሆነ ዶ/ር ሰውአለ ይጠቁሙና “የመንግሥት ምክንያት የሚያሳምን አይደለም” ይላሉ።

የብድር ወለድን አለመክፈል ጉዳት እንደሚያስከትል አሳስበው መንግሥት የሚጠበቅበትን ክፍያ እንዲከፍልና ድርድሮችን ጎን ለጎን እንዲያካሂድ ዶ/ር ሰውአለ መክረዋል።

አሥር ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የአንድ ቢሊየን ዶላር ዩሮ ቦንድ ሽያጭ ሙሉ ክፍያንም ኢትዮጵያ በቅርቡ ማጠናቀቅ ይጠበቅባታል።

ሃገሪቱ ከውጭ አበዳሪ ሃገሮችና ተቋማት ያለባት ዕዳ ወደ ሰላሣ ቢሊየን ዶላር እየተጠጋ ነው።