በተጠናቀቀው የአውሮጳውያኑ 2023፣ ኤል ኒኞ እና የአየር ንብረት ለውጥ የከፋ አደጋን አስከትለዋል

Your browser doesn’t support HTML5

በአውሮጳውያኑ የዘመን አቆጣጠር እየተሸኘ ያለው የ2023 የሙቀት መጠን፣ በመላው ዓለም በከፍተኛነቱ ተመዝግቧል። የሙቀት መጠን መመዝገብ ከጀመረ ወዲህ የታየ ከፍተኛው መጠን እንደኾነም ተነግሯል። አንዳንድ ሳይንቲስቶች ደግሞ፣ በ125ሺሕ ዓመታት ውስጥ ያልታየ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንደኾነ ይገልጻሉ።

በካናዳ የደን እሳት፣ በሊቢያ ጎርፍ፡- የአየር ኹኔታው አደገኛ በኾነበት የዘንድሮ ዓመት የታዩ ክሥተቶች ናቸው። 2023፤ እስከ ዛሬ በፍጥረተ ዓለሙ በተመዘገበው የአየር ንብረት፣ ከፍተኛ ሙቀት የታየበት ዓመት ተብሉ በታሪክ ይመዘገባል። ይኸውም፣ ከሰኔ እስከ ኅዳር ያለው እያንዳንዱ ወር፣ እስከ ዛሬ ታይቶ የማያውቅ ከፍተኛ ሙቀት ተመዝግቦበታል፡፡

በአሜሪካ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር ከፍተኛ የሳይንስ ባለሞያ ሳራ ካፕኒክ ፤ “ያለፈው ሐምሌ እጅግ ሞቃታማው የሐምሌ ወር ኾኖ ዐልፏል። ሙቀቱ የጨመረውም በከፍተኛ መጠን ነው።” ይላሉ።

ያለፈው መስከረም ሙቀት፣ እስከ ዛሬ ካለፉት የመስከረም ወራት ኹሉ ሞቃት መኾኑ እጅግ እንዳስገረማቸው፣ የአየር ንብረት ሳይንስ ባለሞያዎች ተናግረዋል።

ከሰው ልጅ ያልተቋረጡ ክንዋኔዎች አንዳንዶቹ፣ ለዓለም ሙቀት መጨመር አስተዋፅኦ ሲያደርጉ፣ ኤል ኒኞ የተሰኘው ክሥተትም በመላው ዓለም ግመቱ እንዲጨምር አድርጓል።

በአውሮፓ ኅብረት የ“ኮፐርኒከስ የአየር ንብረት ለውጥ አገልግሎት” የተባለው ተቋም ባልደረባ ሰማንታ በርጊስ፣ “ይህ ተጨማሪ ሙቀት በከባቢ አየር ውስጥ መኖሩ፣ ተጨማሪ ኀይል እንዲፈጠር አድርጓል። በመኾኑም፣ ከበድ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ይከሠታሉ።” ይላሉ።

እያንዳንዱ መጥፎ የአየር ክሥተት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የመጣ አይደለም። ይኹንና፣ የዓለምን የአየር ኹኔታ የሚከታተሉ የሳይንስ ሰዎች፣ በእነዚኽ ክሥተቶች ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ አሻራን አግኝተዋል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር፣ ታይላንድ እና ላኦስ፣ ከፍተኛ የአየር ሙቀት አስመዝግበዋል። የሳይንስ ባለሞያዎቹ እንደሚሉት፥ ለሙቀት መጠኑ መጨመር፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ውጪ የሚከሠትበት ዕድል አይኖርም።

በዚኹ ወር፣ የምዕራብ ሜዲትሬንያን ሐሩር፣ እስከ አኹን የተመዘገቡ የሙቀት መጠኖችን ሰብሮ አልፏል።

ደቡብ አውሮፓ፣ ባለፈው ሐምሌ በሙቀት ስትቀቀል ነበር። ቻይና እንዲሁም በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መካከል የሚገኘው ደንበርም እንዲሁ። በደቡብ ምዕራብ አሜሪካ የምትገኘው የፊኒክስ ከተማ፣ ለተከታታይ 31 ቀናት 43ነጥብ3 ዲግሪ ሴልሲየስ አስመዝግባለች፡፡ ይህም፣ እስከ አኹን ከታየው ከፍተኛው ነው።

“መቸም፣ ይህ ክብረ ወሰን ሰዎች ሊሰብሩት የሚሹት አይደለም። በፊኒክስ የሚኖሩ ሰዎች፣ በክሥተቱ ደስተኞች አይደሉም።” ያሉት በአሪዞና ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮፌሰር ካቲ ጄከብስ ናቸው።

ለእነዚኽ ሙቀቶች መጨመር፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ውጭ የሚጠቀስ መንሥኤ ይኖራል ተብሎ እንደማይታሰብ፣ የዓለም የአየር ኹኔታን የሚከታተለው ተቋም ያስታውቃል። ክሥተቱም፣ እየጋመች በመጣችው ሉላዊቷ ዓለም፣ በየ5፣ 10 ወይም 15 ዓመታት ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠበቃል።

ከፍተኛ ሙቀት፥ አፈርንና ዕፀዋትን በፍጥነት ያደርቃል። ይህም፣ በምሥራቅ ካናዳ የተነሣውን የዱር እሳት የማስከተል ዕድልን፣ ቢያንስ በሰባት ዕጥፍ እንዲጨምር ሲያደርግ፣ ኀይለኝነቱም በ50 በመቶ እንዲጨምር አድርጓል።

በሶርያ፣ ኢራቅ እና ኢራን ድርቁ ሲበረታ፣ በሶማሊያ እና በአፍሪካ ቀንድ ደግሞ የምግብ ዋስትና ቀውስን ፈጥሯል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ሶማሊያ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲፈጠር ያደረገችው አስተዋፅኦ የለም፤ ነገር ግን ከዋና ተጠቂዎቹ አንዷ ናት፡፡” ብለው ነበር።

የአየር ንብረት ለውጥ፥ ድርቅን ያባብሳል፤ የጎርፍ ሙላትንም እንዲሁ። ምክንያቱም ሞቅ ያለ አየር፣ ተጨማሪ እርጥበት ይይዛል። ያ ደግሞ ከባድ ዝናም ያስከትላል።

ልክ ባለፈው መስከረም፣ በሊቢያ የደርና ግድብ ፈርሶ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደገደለው ማለት ነው። የአየር ንብረት ባለሞያዎች እንደሚሉት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ አደጋ የመከሠቱ ዕድል እና የጥንካሬው መጠን በ50 በመቶ ጨምሯል።

በኅዳር ወር፣ በአፍሪካ ቀንድ የተከሠተው ዝናም ኀይለኛነቱ ከወትሮው በሁለት ዕጥፍ የጨመረ ነበር።

“ወርልድ ዌዘር አትሪቢዩሽን” የተሰኘው ተቋም መሪው ፍሬድሪክ ኦቶ ድርቁ፤ በአካባቢው ያሉ ሰዎች የሚፈተኑበትን የአደጋ ጫፍ እንዳሳያቸው ተናግረዋል።

አክለውም፤ “በዚያው ላይ ጎርፉ ሲታከልበት፣ በዓለም የሚኖሩ ሰዎች በቀላሉ ከማይቋቋሙት የአደጋ አፋፍ ላይ ያደርሳቸዋል።

የዕፀዋት እና የእንስሳት ቅሪቶችን በማቃጠል ነዳጅ ማምረታችንን እስከቀጠልን ድረስ፣ አደጋዎቹ እንደሚደጋግሙን የታወቀ ነው።” ብልዋል።

የአየር ኹኔታ ትንበያ ላይ የተሰማሩ ባለሞያዎች እንደሚሉት፣ የኤል ኒኞ ተጽእኖ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ላይ ሊቀንስ ይችላል።

ያም ኾኖ፣ የአየር ንብረት ለውጡ ጋብ ይል እንደኹ፣ ምንም ምልክት እየታየ አይደለም። ሉላዊቷን ዓለም እያጋምን በቀጠልን ቁጥር፣ አልፎ አልፎ የምናየው አደገኛ የአየር ክሥተት፣ በአጭር ጊዜ ልዩነት እየደጋገመን አዘቦታዊ ሳይኾን የሚቀር አይመስልም፡፡

የቪኦኤው ስቲቭ ባራጎና የዓመቱን ሙቀት በተመለከተ ያጠናቀረው ሪፖርት ነው። እንግዱ ወልዴ ወደ ዐማርኛ መልሶታል።