በድንገተኛው የአጣዬ የተኩስ ልውውጥ የብሔር ግጭት እንዳያገረሽ ነዋሪዎች ሰግተዋል

Your browser doesn’t support HTML5

በዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሰሞኑን ተቀስቅሶ በነበረው የጸጥታ ችግር፣ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና ብዙዎች ተፈናቅለው እንደነበር፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው ነዋሪዎቹ፣ በመከላከያው እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰው የተኩስ ልውውጥ፣ ከዚኽ ቀደም ተፈጥሮ የነበረው የብሔር ግጭት ዳግም እንዳያገረሽ ስጋታቸውን አመልክተዋል፡፡

የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ደግሞ፣ ንጹሐን ሰዎች እንደተገደሉና እንደተፈናቀሉ ገልጾ፣ ቁጥሩ ግን ምርመራ ከተደረገ በኋላ ይፋ እንደሚኾን ጠቁሟል፡፡

ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አጎራባች ቀበሌዎች ጋራም ግጭት እንዳይቀሰቀስ፥ ከፖለቲካ አመራሩ፣ ከአገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋራ ውይይት በመደረጉ፣ ከተማዋ እና አካባቢዋ በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ እንደሚገኙ፣ የከተማዋ ከንቲባ አስታውቀዋል፡፡

በዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ እና አካባቢዋ፣ ባለፈው ኅዳር 30 ቀንና ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በመከላከያ ኀይል እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ተቀስቅሶ እንደነበር፣ ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በመንግሥት ሥራ እንደሚተዳደሩ ያስታወቁ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡

“እሁድ ዕለት ምሽት ላይ ወደ 11፡30 አካባቢ ጀምሮ ከከተማው ወጣ ያለ ቦታ ሞሎ እሚባል አካባቢ ጋር የነበረ ውጊያ ወደ ከተማ ተጠግቶ እየመሸ ሲሄድ 12 ሰዓት አካባቢ ሙሉ በሙሉ ከተማ ውስጥ ገብቶ ተኩስ ነበረ፡፡ እና ከዛ በኋላ ታጣቂው ተመልሶ ከከተማ የወጣ ሲሆን፣ ከብሔረሰብ ዞን ራሳችንን ለመከላከል በሚል እንደገና ሌላ ተኩስ ወደ ከተማው መተኮስ ጀምረው ተጠግተው ነበረ፡፡” ያሉት እኚኽ የከተማ ነዋሪ፤ በሁለቱ መካከል ሌላ የብሔረሰብ ፀብ እንዳይቀሰቀስ፣ መከላከያ ሠራዊት የማረጋጋት ሥራ እየሠራ እንደነበር ጠቁመዋል።

አክለውም፤ “እስከ ትላንትና ጠዋት ድረስ በጣም ከፍተኛ የሆነ ተኩስ ነበረ፡፡ ሠዉ ሙሉ በሙሉ አዳሩን ሲጓዝ ነው ያደረው፡፡ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውጣን፣ አቅመ ደካሞች በሙሉ ሲንገላቱ ነው ያደሩት፡፡ ደግሞ ይሄ ተደጋጋሚ ነገር ስለሆነ፣ ህዝቡ በጣም ያልተገባ መንገላታት ውስጥ እያገባ ነው።” ብለዋል።

በተመሳሳይ ምክንያት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ፣ አካባቢው ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጋራ አጎራባች በመኾኑ፣ የሁለቱ ኀይሎች የተኩስ ልውውጥ፣ ለሌላ የብሔር ግጭት ምክንያት ሊኾን ይችላል፤ በሚል ስጋት በሽሽት ላይ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው እንዳለፈ አመልክተዋል፡፡

ምሽት ላይ ላይ ፋኖዎቹ ከላይ ከመከላከያ ጋር እየተታኮሱ እንደነበር የጠቆሙት እኚህ ነዋሪ፤ “ፋኖዎቹ ገብተው ወጡ፡፡ እና ህዝቡ ከንጋት ጀምሮ ወጥቶ ነበረ፡፡ አንድ አብዱራህማን የሚባል ባለ ባጃጅ ነበረ፤ በሱ ሽሽት ሲሄዱ ጧት ላይ ተኩሱ መታቸው፤ 3 ሰዎች ሞቱ፡፡ ከከተማው ከምኑም 11 ሰው አካባቢ ሕይወቱ አልፏል፡፡” ብለዋል።

የሟቾችን ቁጥር፣ ከአጣዬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለማረጋገጥ፣ ወደ ተሰጠን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዲሬክተር ስልክ ብንደውልም ሊመልስልን አልቻለም፡፡

የአጣዬ ከተማ ዋና ከንቲባ አሳልፍ ደርቤ፣ በሰሞኑ የከተማዋ የጸጥታ ችግር፣ የሞት እና የመፈናቀል አደጋዎች እንደነበሩ ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳዳር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ ዓሊ፣ በአጣዬው የተኩስ ልውውጥ፣ በአጎራባች የኦሮሞ ብሔረሰብ ቀበሌዎች ላይ ስጋት ፈጥሮ እንደነበርና ከሰሜን ሸዋ እና ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተውጣጡ የአገር ሽምግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና አመራሮች ጋራ በተደረገው ምክክር፣ ችግሩ ሳይባባስ መቆጣጠር እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡

ዛሬ እና ትላንት፣ የአጣዬ ከተማ እና አካባቢዋ አንጻራዊ ሰላምን ቢያስተናግዱም፣ የተኩስ ልውውጡ በድንገት ስለሚቀሰቀስ፣ ነዋሪው ሙሉ በሙሉ ከስጋት ነጻ እንዳልወጣ፣ አስተያየት ሰጭዎቹ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት፣ “በየትኛውም ኢ-መደበኛ አደረጃጀት እና የትጥቅ ትግል ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ለሚገኙ” በማለት ባወጣው መግለጫ፣ በመጪዎቹ ሰባት ቀናት ውስጥ፣ ባሉበት አካባቢ ተለይተው በተዘጋጁ የመሰብሰቢያ ስፍራዎች በመሔድ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ያስቀመጠው ጊዜ ገደብ፣ ዛሬ ሦስተኛ ቀን ኾኖታል፡፡

ይኹን እንጅ፣ በክልሉ ላለፉት አራት ወራት የዘለቀው የጸጥታ ችግር፣ ለበርካቶች ሞት፣ የአካል ጉዳት እና መፈናቀል ምክንያት መኾኑን እንደቀጠለ ነው፡፡