ከፍተኛ የምርጫ ፉክክር ይኖርባቸዋል በተባሉ በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ የእስልምና መሪዎች፣ ለፕሬዝደንት ጆ ባይደን የነበራቸውን ድጋፍ እንደሚስቡ አስታውቀዋል። ምክንያት ያሉትም ፕሬዝደንቱ በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው።
በሚቺጋን የሚገኙ ዲሞክራቶች ፕሬዝደንቱ የእስራኤል እና ሐማስን ጦርነት የያዙበት መንገድ፣ በመጪው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ የዓረብ አሜሪካውያንን ድምፅ ሊያሳጣቸው እና የምርጫውን ውጤትም ሊቀየረው እንደሚችል ዋይት ሃውስን አስጠንቅቀዋል።
በአሜሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዓረብ አሜሪካዊያን በሚገኙባት ሚቺጋን የተሰባሰቡትና ከሚነሶታ፣ አሪዞና፣ ዊስከንስን፣ ፍሎሪዳ፣ ጆርጂያ፣ ነቫዳ፣ እና ፔንስልቬኒያ የተሰባሰቡት ሙስሊም መሪዎች፣ ለባይደን የነበራቸውን ድጋፍ በሚያቆሙበት እና በጋዛ የተኩስ አቁም ስለሚኖርበት ጉዳይ ውይይት ተቀምጠዋል።
ኮንፈረንሱ እንዲዘጋጅ ድጋፍ ካደረጉት ውስጥ፣ በሚነሶታ ነዋሪ የሆኑት ጄይላኒ ሁሴን እንደሚሉት፣ ባይደን ተኩስ የማቆም ጥሪ ለማድረግ ፍላጎት ባለማሳየታቸው፣ ከአሜሪካ ሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መጠገን በማይችልበት ሁኔታ ተሰብሯል።
“ቤተሰቦች እና ሕፃናት በምንከፍለው የታክስ ገንዘብ እንዲጠፉ እየተደረገ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል ጄይላኒ ሁሴን።