ትላንት የላሊበላን ከተማን በከፊል ተቆጣጥረው የነበሩት የፋኖ ታጣቂዎች፣ እየለቀቁ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የፌዴራሉ ጦር ኃይሎች፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ከተማዋን መልሰው እንደተቆጣጠሩ፣ ነዋሪዎች ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
ፍልፍል አብያተ መቅደሶቹ የሚገኙባትና በዩኔስኮ ቅርስነት የተመዘገበችው የላሊበላ ከተማ፣ በዚኽ ዓመት፣ በተደጋጋሚ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች መካከል የውጊያ ዐውድማ ኾናለች፡፡
ትላንት ረቡዕ በዋለው ውጊያ፣ የፋኖ ታጣቂዎች አብዛኛውን የከተማዋን ክፍል ተቆጣጥረው እንደነበር፣ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ፣ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገረው፣ የፋኖ ታጣቂዎች ሌሊቱን ለቀው በመውጣታቸው፣ የመከላከያ ኃይል ዛሬ ከተማዋን ተቆጣጥሯል።
ሌላው ነዋሪ ደግሞ፣ “እስኪነጋጋ ድረስ ከተማዋ በፋኖ ቁጥጥር ሥር ነበረች፡፡ ኾኖም፣ ጠዋት ስንነቃ፣ ፋኖ ለቅቆ እየወጣ ነበር፤” ብሏል። “በአሁን ሰዓት፣ በመንገዱ ላይ የማየው የመከላከያ ኃይሉን ነው፤” በማለትም አክሏል።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉት ሁለቱ ነዋሪዎች፣ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ዛሬ ሐሙስ ዐዲስ ግጭት አልነበረም።
ትላንት በነበረው ውጊያ፣ የመከላከያ ኃይሎች፣ በከተማዋ ዳርቻ ወደሚገኝ መደባቸው አፈግፍገው እንደነበር፣ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግሥት እና የመከላከያ ተወካዮች፣ እንዲሁም የክልሉ ባለሥልጣናት፣ በኹኔታው ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለተላከላቸው መልዕክት መልስ እንዳልሰጡ፣ ዜና ወኪሉ ገልጿል።
በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኘው የዐማራ ክልል፣ ለጋዜጠኞች ክፍት ባለመኾኑ፣ ኹኔታውን በገለልተኛ ወገን ለማጣራት አዳጋች እንደኾነበት በዘገባው ተመልክቷል።