የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በጋዛ ሰርጥ የሚገኝን የስደተኞች መጠለያ ሲደበድቡ 40 የሚሆኑ ሰዎች ሲሞቱ፣ ሌሎች በደርዘን የሚቆጠሩት ደግሞ እንደቆሰሉ የፍልስጤማውያኑ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ጥቃቱ የመጣው ሲሊቭሎች ሰብዓዊ ርዳታ ያገኙ ዘንድ ግዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲኖር አሜሪካ እየጠይቀች ባለችበት ወቅት ነው። እስራኤል ጥያቄውን አትቀበልም።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አክሎም፣ ግጭቱ ከጀመረ አንስቶ 9ሺሕ 700 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት አራተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረበት በዚህ ወቅት፣ 2ሺሕ 500 የሚሆኑ የሐማስ ኢላማዎችን መምታቷን እስራኤል ዛሬ አስታውቃለች፡፡
ድብደባዎቹ የተደረጉት በምድር፣ በአየር እና በባህር ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ እንደሆነም እስራኤል አስታውቃለች፡፡
የሐማስ ወታደራዊ ማሠልጠኛዎች፣ ማዛዣ ጣቢያዎች፣ እና ሌሎች ሐማስ የሚጠቀምባቸው መሠረተ ልማቶች እንደተመቱ እስራኤል ጨምራ አስታውቃለች፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፣ ጦርነቱ ከጀመረ አስንቶ በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ 102 የጤና ተቋማት ላይ ጥቃት መድረሱን፣ በዚህም ምክንያት 504 ሰዎች መገደላችውን እና 459 የሚሆኑ መቁሰላቸውን፣ እንዲሁም 39 የጤና ማዕከላት እና 31 አምቡላሶችም መውደማቸውን አስታውቋል።
አብዛኞቹ ጥቃት የደረሰባቸው ሆስፒታሎች በጋዛ ከተማ የሚገኙ እንደሆኑ የጤና ድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አሚሃይ ኤሊያሁ የተባሉ የቅርስ ሚኒስትር “ጋዛ ላይ የኑክሌር ቦምብ ሊጣል ይችላል” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ነታንያሁ ከካቢኔ ስብሰባዎች አግደዋቸል። የሚኒስትሩ አስተያየት እውነታ ላይ የተመሠረት አለመሆኑን ነታንያሁ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስታውቀዋል። ሚኒስትሩ አሚሃይ ኤሊያሁ የጦር ካቢኔ አባል እንዳልሆኑ ታውቋል።