በእስር ላይ ያሉት የቀድሞው የሐዋሳ ከንቲባ ሰብአዊ መብት እየተጣሰ ነው፤ ሲሉ ወንድማቸው ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

ለሕክምና ከሔዱበት ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ፣ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተይዘው የታሰሩት፣ የቀድሞ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ጸጋዬ ቱኬ፣ ሕገ መንግሥታዊ እና ሰብአዊ መብቱ እየተጣሰ ነው፤ ሲሉ፣ ወንድማቸው ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ።

አቶ ጸጋዬ፣ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አባል ኾነው ሳለ ያለመከሰስ መብታቸው እንደተጣሰ የጠቀሱት ወንድማቸው ተክሌ ቱኬ፣ ከታሰሩ ሳምንት ቢኾናቸውም፣ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና የሕክምና ክትትልም እንደተከለከሉ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት፣ ትላንት ማክሰኞ ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ፣ የአቶ ጸጋዬ ቱኬን ጨምሮ፣ የሌሎች ሦስት የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት እንዲነሣ ወስኗል።

የአሜሪካ ድምፅ በውሳኔው ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር እና የሰብአዊ መብቶች ባለሞያ በፈቃዱ ድሪባ፣ በወንጀል እጅ ከፍንጅ እስካልተያዙ ድረስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ከሕግ አግባብ ውጭ እየተያዙ የሚደርስባቸው የመብቶች ጥሰት፣ ሥርዐተ አልበኝነት እንደሰፈነ ማሳያ ነው፤ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም፣ ባለሥልጣናቱ፥ ሕገ መንግሥታዊነትን ለማክበር እና ለማስከበር ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እስከሌላቸው ድረስ፣ በሒደት የሚከተለው ቀውስ የማያስቆሙት እንደኾነ፣ ባለሞያው አሳስበዋል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡