የሃማስን ጥቃት እስካሁን ያላወገዘችው ቻይና አጋርነቷን እንድታሳይ እሥራዔል አሳሰበች

  • ቪኦኤ ዜና

ፋይል - ቻይና ቤጂንግ በሚገኘው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ከመጀመሩ በፊት፣ በምስሉ ላይ የቻይና እና የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ አርማ ይታያል፣ ኅዳር 11/ 2008

የሃማስ ታጣቂዎች በእሥራዔል ላይ ላደረሱት ድንገተኛ ጥቃት፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሁለቱም ወገኖች እራሳቸውን እንዲቆጣጠሩ ጥሪ በማድረግ፣ የሩሲያን አቋም የሚያንጸባርቅ ምላሽ ሰጥታለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ "በአሁኑ ወቅት በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል ያለው ውጥረት እና ጸብ መባባስ ቻይናን በጣም አሳስቧታል።
ሲቪሎችን ለመጠበቅ እና ሁኔታው እንዳይባባስ ለማድረግ፣ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት እንዲረጋጉ፣ ራሳቸውን እንዲቆጣጠሩ እና ፀበኝነት እንዲያቆሙ እንጠይቃለን" ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለው "ከግጭት ለመውጣት ዋንኛው መንገድ የሁለት-መንግስት መፍትሄን መተግበር እና ነፃ የሆነች ፍልስጤምን እንደ ሀገር መመስረት ነው" ብለዋል።
መግለጫውን ተከትሎ፣ ቤይጂንግ የሚገኘው የእስራዔል ኤምባሲ ባለስልጣን የሆኑት ዩቫል ዋክስ፣ ቀድሞ ትዊተር በመባል ይጠራ በነበረው ኤክስ የማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ በፃፉት መልዕክት፣ እሥራዔል፣ ሃማስ ላደረሰው ጥቃት ከቻይና ጠንካራ ውግዛት ጠብቃ ነበር ብለዋል
"ሰዎች እየተገደሉ እና በየጎዳናው እየታረዱ፣ ስለሁለት-መንግሥት መፍትሄ ጥሪ የሚደረግበት ጊዜ አይደለም" ሲሉም እሁድ እለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቻይና በጋዛ የሚገኘውን ሃማስን በአሸባሪነት የማትፈርጅ ሲሆን፣ እንደ ተቃዋሚ ድርጅት ትቆጥረዋለች። የእሥራዔል ኤምባሲም እንዲሁ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ "ቻይና በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለእሥራዔል አጋርነት እና ድጋፍ እንደምትሰጥ ተስፋ እናደርጋለን" በማለት ቤይጂንግ ከእሥራዔል ጋር እንድትቆም ጥሪ አቅርቧል።
በቻይና እና በእስራዔል መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ባለፉት ሦስት አስርት ዓመት ውስጥ እያደገ ቢሄድም፣ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ፖለቲካዊ አለመግባባት ግን እንደቀጠለ ነው።
እነዚህ አለመግባባቶችም፣ ከፍልስጤም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ያለውን ክፍፍል፣ ቻይና እንደ ኢራን ካሉ የእሥራዔል ጠላቶች ጋር ያላትን ግንኙነት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተመለከተ እሥራዔል የምታነሳቸው ከደህንነት ጋር የተያያዙ ስጋቶችን ያካትታሉ።
በጆርጅ ታውን ዩንቨርስቲ የእስያ ጥናቶች ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዴኒስ ዊልደር ለአሜሪካ ድምፅ ሲያስረዱ "ቻይና ከእሥራዔል ጋር ጠንካራ ግንኙነት ቢኖራትም ፣ ግንኙነቱ ወታደራዊ ቴክኖሎጂን ጨምሮ፣ እሥራዔል ቴክኖሎጂን ወደ ቻይና ለማስተላለፍ ባላት ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው" ይላሉ።
"የኢኮኖሚ ትስስሩ ጠንካራ ቢሆንም፣ ቻይና እና እሥራዔል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ልዩነት አላቸው" የሚሉት ዊልደር "ለምሳሌ ቻይና ከኢራን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት። ቻይና ፍልስጤም ራሷን የቻለች ሀገር እንድትሆን ሁሌም ስለምትደግፍ አብዛኞቹን የእሥራዔልን ፖሊሲዎች በፖለቲካዊ መንገድ ትቃወማለች" ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ቻይና የእስራኤል እና የፍልስጤምን የሰላም ስምምነት መሸምገል ስለመቻሏ ጥርጣሬ አላቸው። ቻይና በመጋቢ ወር በሳዑዲ እና ኢራን መካከል ሻክሮ የነበረው ግንኙነት እንዲለሳልሳ አደራድራ ነበር።

መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገው ካርኔጅ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የሰላም ተቋም ውስጥ ከፍተኛ አጥኚ አሮን ዴቪድ ሚለ፣ "ቻይና እስከተቻላት እንደፈለገች አቋማን ማስተካከል የምትችልበትን ሁኔታ መጠበቅ ትፈልጋለች" ብለዋል።

አክለውም "እንደውም 'ምንም እንኳን እውን ሊሆን የማይችል ቢሆንም' እሥራዔልን እና ፍልስጤማውያንን ማሸማገል ትችል እንደሆነም ተስፋ ልታደርግ ትችላለች" ሲሉ ተናግረዋል።

የታይዋን የውጭ ጉዳሃን ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን "የሽብር እና የኃይል ጥቃቶችን በጥብቅ እንደምታወግዝ" አስታውቃለች።

የታይዋን ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግ-ዌንም እንዲሁ በኤክስ ላይ በፃፉት መልዕክት "ሃማስ በእሥራዔል እና በእሥራዔላውያን ላይ ባደረሰው ጥቃት ለተጎዱ ወይም ዘመዶቻቸውን ላጡ በሙሉ፣ በታይዋን ህዝብ እና መንግስት ስም የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ" ብለዋል።