በመቐለ ከተማ የታሰሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአስከፊ ችግር ላይ እንደሚገኙ ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

- ቅሬታውን እንደማያውቀው የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ገለጿል

“በመቐለ ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኙ” የገለጹ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና ቤተሰቦቻቸው፣ በችግር ላይ እንደኾኑ ተናገሩ፡፡የመከላከያ ሠራዊቱ አባል እንደኾነ የገለጸ አንድ አስተያየት ሰጭ፣ ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ እንደቆየ ገልጾ፣ በከፍተኛ የምግብ እና የሕክምና እጥረት እንደቆዩ ተናግሯል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ያለአንዳች ታስረው እንደሚገኙም ገልጿል፡፡

የታሳሪ ወታደሮች ቤተሰብ አባላትም፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በአሁኑ ወቅት ያለበቂ ምግብ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ በእስር እየተሠቃዩ እንዳሉ ገልጸው፣ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሹ አመልክተዋል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡን የሠራዊቱ ቤተሰቦች መካከል፣ የቤተሰብ ወገን የኾኑ ወታደሮች ሕይወታቸው በጦርነቱ እንዳለፈ በመንግሥት መርዶ ከተነገራቸው በኋላ፣ በሕይወት መኖራቸውን እንዳረጋገጡ የገለጹም ይገኛሉ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በየዓመቱ በሚያወጣው የሀገራት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርቱ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት፣ በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች አካባቢዎች በተዛመተው ጦርነት፣ በሁሉም ተፋላሚ ኀይሎች፣ የተለያዩ የጦር ወንጀሎች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸሙ መግለጹ ይታወሳል። ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችም፣ ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ሲያወጡና ጉዳዩ በገለልተኛ መርማሪ ቡድን እንዲያጣራ ሲጠይቁ እንደቆዩ አይዘነጋም።

ታሳሪዎቹን የመጎብኘት እና በተቻለ መጠን ከቤተሰቦቻቸው ጋራ በስልክ የማገናኘት ሥራ እያከናወነ እንደኾነ ያስታወቀው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ በእስር ቤቶች ውስጥ ስላለው ኹኔታ ግን፣ በይፋ አስተያየት መስጠት እንደማይችል ገልጿል። በመቐለ የሚገኙ የጦር ምርኮኞች ያቀረቡትን ቅሬታ እንደማያውቀው የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ገለልጿል።

በሌላ በኩል በመቐለ ከተማ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የምግብ እጥረት እና የሕክምና አገልግሎት እንደማያገኙ ጠቅሰው ያቀረቡትን አቤቱታ እንደማያውቀው፣ የትግራይ ክልል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን የታራሚዎች ጥበቃ እና ደኅንነት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዲሬክተር ኮማንደር ዘሥላሰ ታደሰ፣ የጦር ምርኮኞቹ ስላቀረቡት የምግብ እጥረት ከአሜሪካ ድምፅ ተጠይቀው በጽሑፍ በሰጡት ምላሽ፣ “እንዲህ ዓይነት ቅሬታ፣ ወደ እኛም ይኹን ወደ መቐለ ማረሚያ ቤት እስከ አሁን አልቀረበም፤” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

ኮማንደር ዘሠላስ በጽሑፍ ምላሹ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ ከጠርነቱ በፊት፣ በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ታራሚዎች፣ ለአንድ ሰው በቀን 22 ብር በኾነ በጀት አገልግሎት ሲያገኙ እንደነበር አውስተዋል፡፡

ኾኖም ግን፣ ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እስኪዋቀር ድረስ፣ የታራሚዎቹ አገልግሎት እንዲቀጥል የተደረገው፣ ከሕዝብ በተዋጣ ገንዘብ እንደነበረና ለሁሉም ሰው የሚዳረስ እንዳልነበር፣ ኮማንደር ዘሥላስ አስረድተዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በጀት ተፈቅዶለት ሥራ ከጀመረ በኋላ ግን፣ በማረሚያ ቤቱ፣ ለአንድ ሰው በቀን 53 ብር ከ45 ሳንቲም ተፈቅዶ፣ አገልግሎት እየተሰጣቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ዲሬክተሩ ገለጻ፣ ይህም በጀት፣ በሀገር ደረጃ ለአንድ ሰው ከሚመደበው 36 ብር አኳያ ሲታይ የተሻለ ነው፡፡ አያይዘውም፣ አገልግሎቱን ለምርኮኞቹ እያቀረብን ያለነው፣ ሰብአዊ መብቶቻቸውን በአግባቡ ለመጠበቅ እንጂ በቂ ዐቅም ኖሮን አይደለም፤ ያሉት ኮማንደር ዘሥላስ፣ “የተፈናቀለው ሕዝብ በረኀብ እየሞተ ባለበት ወቅት፣ በቂ አገልግሎት አናገኝም፤ ማለት፣ ትክክል አይደለም፤ የሚል አስተያየት አለኝ፤” ሲሉ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱን ቅሬታ ተቃውመዋል፡፡

የጦር ምርኮኞቹ፣ “ከቤተሰቦቻችን ጋራ አንገናኝም” ብለው ያቀረቡትን ቅሬታ አስመልክቶም በሰጡት ምላሽ፣ የመገናኛ መሠረተ ልማቱ በጦርነቱ ስለ ወደመ፣ የስልክ መስመር ካለመኖሩ ጋራ የተያያዘ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ከጦርነቱም በኋላ “ዐዲስ መስመር ለመዘርጋትም ይኹን ለመጠገን የሚያስችል ዐቅምም የለም፡፡ ስለዚህ ይህን አገልግሎት ለወደፊት በምን መልኩ ማሻሻል ይቻላል፤ የሚለውን ለማየት ከመሞከር በስተቀር፣ አሁን ባለው ኹኔታ ምርኮኞችንም ይኹን ሲቪል ታራሚዎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋራ ለማገናኘት የሚያስችል የስልክ አገልግሎት አላስጀመርንም፤” ብለዋል፡፡

ይህም ኾኖ፣ ምርኮኞችን፣ ከቅርብም ይኹን ከሩቅ ቦታ መጥቶ ለመጠየቅ የሚፈልግ ሰው ካለ፣ ባለው አሠራር መሠረት ያለምንም ችግር ማገናኘት እንደሚቻልና የመጎብኘት መብታቸው የተጠበቀ እንደኾነ፣ የዳይሬክቶሬቱ ዲሬክተር አረጋግጠዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፕሪቶርያው ስምምነት ቢቋጭም፣ በጦርነቱ ወቅት፣ “ከህወሓት ጋራ ግንኙነት አላችኹ፤” ተብለው ከታሰሩት የትግራይ ተወላጆች መካከል፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አሁንም ያልተፈቱ እንዳሉ፣ ከዚኽ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

“ሂዩማን ራይትስ ፈርስት” የተባለ ኢትዮጵያዊ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳስታወቀው፣ በጦርነቱ ወቅት በተለያዩ የዐማራ ክልል አካባቢዎች የታሰሩ ንጹሐን የትግራይ ተወላጆች እና ሕጋዊ የዳኝነት አካሔድን ባልተከተለ መንገድ ተከሰው የተፈረደባቸው የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት መፈታት ሲገባቸው፣ አሁንም ድረስ በእስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ አረጋግጫለኹ፤ ብሏል፡፡

ሰዎቹ፣ ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ በእስር ላይ መቆየት እንዳልነበረባቸው ያመለከተው የመብት ተሟጋቹ ድርጅት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት፣ እስረኞቹን እንዲለቋቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. ላይ ተይዘው በአዋሽ አርባ አቅራቢያ ወደሚገኘው “ዐዲስ ራእይ” የወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ እስር ቤት ከተወሰዱ በኋላ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ታስረው የቆዩ 32 የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣በቅርቡ እንደተፈቱም መዘገባችን አይዘነጋም።

/ዘገባው የተሰናዳው በአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢዎች ነው፤ አስማማው አየነው ዘገባውን በድምፅ አቀቦታል/