በአስቸኳይ ዐዋጁ የአዋሽ አርባ እስረኞች ደኅንነት እንደሚያሳስባቸው ቤተሰቦቻቸው ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ በዐማራ ክልል ላይ ከተደነገገውና እንዳስፈላጊነቱ በሌሎች ቦታዎችም ተፈጻሚነት እንደሚኖረው በተገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተይዘው በአዋሽ አርባ የታሰሩ ሰዎችን በአካል እንዳላገኟኛቸውና ደኅንነታቸው እንደሚያሳስባቸው፣ ቤተሰቦቻቸው ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡን የታሳሪ ቤተሰቦች መካከል አንዳንዶቹ፣ ታሳሪ የቤተሰባቸውን አባል በስልክ እንዳገኙ ሲገልጹ፣ ሌሎቹ ደግሞ በስልክም አግኝተዋቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

ታሳሪዎቹ፣ ከአያያዛቸው አንስቶ በእስር ላይ ይደርስብናል ያሏቸውን በደሎች ለመቃወም፣ ዛሬ የረኀብ አድማ እንደሚጀምሩ የሚገልጽ ደብዳቤ፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ተጋርቷል፡፡ ይህም ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል፡፡

ከታሳሪ ጠበቆች አንዱ ሰሎሞን ገዛኽኝ፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ምክንያት ታሳሪዎቹን ማግኘት ስላልተፈቀደላቸው፣ ስለ ረኀብ አድማው በቀጥታ መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ኢሰመኮ ጉዳዩን እንደሚከታተል አስታውቋል፡፡

አድማውንና የታሳሪ ቤተሰቦችን ቅሬታ አስመልክቶ፣ ከመንግሥት አካል ምላሽ እና አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢዜማ ሊቀ መንበር ዶር. ጫኔ ከበደ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ “በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መሠረት በኮማንድ ፖስቱ ተጠርጥረው እንደኾነ አረጋግጫለኹ፤” ሲል ፓርቲው አስታውቋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።