የቡርኪናው ሁንታ ከምርጫ ይልቅ ለጸጥታ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታወቀ

በዋጋዱጉ የሁንታው ደጋፊዎች በሰልፍ ላይ (ፎቶ ፋይል ሮይተርስ)

የዛሬ አንድ ዓመት በቡርኪና ፋሶ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ሁንታ፣ ቃል የተገባው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ለሀገሪቱ ሠላም እና ጸጥታ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ትናንት በመዲናዋ በዋጋዱጉ የመፈንቅለ መንግስት ደጋፊዎች አንደኛ ዓመቱን በማሰብ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ወጣቱ ወታደራዊ መሪ ካፕቴን ኢብራሂም ትራኦሬ፣ ቃል የተገባው ምርጫ የሚካሄደው የጸጥታው ሁኔታ ሲፈቅድ ብቻ ነው ብለዋል።

ትራኦሬ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣኑን የያዙት፣ በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግስት ፕሬዝደንት ሮች ካቦሬን በማስወገድ ለስምንት ወራት ስልጣን ላይ የቆየውን ሁንታ አስወግደው ነበር።

ሕይወትን በሚቀጥፉ የበረታ ሁከቶች የተሰላቹት በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች፣ መፈንቅለ መንግስቱን ሲደግፉ፣ ምዕራቡ ዓለም ግን አውግዞታል።