ግጭት፣ ድርቅ እና መፈንቅለ መንግሥት እያመሳት የምትገኘው አፍሪካ፣ ኒው ዮርክ ላይ እየተካሔደ ከሚገኘው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ለችግሯ መፍትሔ የሚኾን ውሳኔ እንደምትጠብቅ ባለሞያዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ፣ ለበርካታ ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ተፈራ ሻወል እና በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የፖለቲካ ሳይንስ ዋና ተመራማሪው ዶክተር ዳር እስከ ዳር ታየ፣ በጉባኤው ላይ ስላላቸው ምልከታ የአሜሪካ ድምፅ ጠይቋቸዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ፣ ዓለማችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በገጠሟት ዐዲስ ለውጦች እና ተግዳሮቶች ወስጥ እያለፈች ባለችበት በዚኽ ወቅት እንደመካሔዱ መጠን ተጠባቂ እንደኾነ፣ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የፖለቲካ ሳይንስ ዋና ተመራማሪ ዶር. ዳር እስከዳር ታየ ይናገራሉ፡፡
ዶር. ዳር እስከዳር፣ ዓመታዊው ጠቅላላ ጉባኤ፣ የአባል ሀገራቱ የግንኙነት መድረክ ኾኖ እንደሚያገለግል ጠቅሰው፣ የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውንና የገጠሟቸውን ችግሮች፣ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንዲኾኑ የሚያቀርቡበትም ጭምር ነው፤ ይላሉ፡፡
ብዙ ጊዜ፣ በጠቅላላ ጉባኤው የውይይት አጀንዳ እና ትኩረት ላይ ልዩነቶች የሚስተዋሉት፣ በዚኽ ምክንያት እንደኾነ የሚያስረዱት ዳርስከዳር፣ ዘንድሮም ይህ እንደሚጠብቅ ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ፣ በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ሥርዐቶች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ተፈራ ሻወል በበኩላቸው፣ በመድረኩ የሚነሡ የውይይት አጀንዳዎች እና የውሳኔአቸው ተግባራዊነት፣ በዓለም አቀፍ ሥርዐቱ ላይ ከፍ ያለ ተጽእኖ ባላቸው ሀገራት ፍላጎት እንደሚወሰን ያስገነዝባሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሥርዐት፣ ሰላምንና ደኅንነትን የሚያስጠብቅ ባለብዙ ወገን ተቋም እንደኾነ ይታመናል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን፣ ከውክልና እና ገለልተኝነት ጋራ በተያያዘ፣ በአባል ሀገራቱ ትችቶች ሲዘነሩበት ይስተዋላል፡፡
እነዚኽ ትችቶች እና ጥያቄዎችም፣ በጠቅላላ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ ወቅት ጎላ ብለው ይሰማሉ፡፡ ዶር. ዳር እስከዳር ታየ እንደሚሉት፣ በተለይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ባላቸው የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና ላይ የሚነሡት ትችቶች፣ አሁን በብዛት እየተስተጋቡ መጥተዋል፡፡
በርግጥ፣ በዩክሬንና በሩስያ መካከል እየተካሔደ በሚገኘው ጦርነት ደረጃ፣ ዓለምን በሁለት ጎራ የሚያሰልፉ ችግሮች ሲከሠቱ፣ የተቋሙን ተኣማኒነት እንደሚፈትን የሚጠበቅ እንደኾነ፣ አምባሳደር ተፈራ ሻወል ይቀበላሉ፡፡ ይህም ኾኖ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከምሥረታው ጀምሮ፣ በሰላም ማስከበር በኩል፣ ለዓለም ሰላም እና ደኅንነት ያበረከተውን አስተዋፅኦ ሊሽር እንደማይችል፣ አምባሳደሩ ይሞግታሉ፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ የውክልና አባልነትን የሚፈቅድ ማሻሻያ እንዲደረግ ከሚጠይቁት መካከል፣ የአፍሪካ ኅብረት እና አባል አገራቱ ይገኙበታል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ዳር እስከዳር ታየ ግን፥ ግጭት፣ ድርቅ እና መፈንቅለ መንግሥት እያመሳት የምትገኘው አፍሪካ፣ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ 78ኛ ዓመታዊ የመሪዎች ስብሰባ፣ ለችግሯ የሚበጃት መፍትሔ የምትጠብቅበት ጊዜ እንደኾነ ያመለክታሉ፡፡
በይፋ ከተጀመረ ቀናትን ባስቆጠረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ 78ኛው ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ 150 የዓለም ሀገራት በመሪዎቻቸው ደረጃ ተወክለው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በተለመደው የተቋሙ አሠራር፣ መሪዎቹ በተመደበላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ንግግራቸውን ለጠቅላላ ጉባኤው ማሰማታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የተመድ መሥራች የኾነችው ኢትዮጵያም፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አቶ ደመቀ መኰንን በኩል፣ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተወክላለች፡፡
አቶ ደመቀ፣ ከጠቅላላ ጉባኤው ጎን ለጎን ከትላንት በስቲያ ረቡዕ፣ መስከረም 9 ቀን በተካሔደው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፣ ምክር ቤቱ ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖረው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም፣ የታቀደውን ዘላቂ ልማት እና እድገት እንዲያሳኩ፣ አስቸኳይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ይከታተሉ።
Your browser doesn’t support HTML5