በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ቅበት ከተማ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ላይ ደርሷል ያለውን ልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ማጣራቱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ መንግሥት ወንጀል ፈፃሚዎችን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ።
የቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ምደባም፥ የሠራተኛውን ፍላጎት፣ የቤተሰብን አንድነት፣ የማኅበራዊ እና የጤናን ኹኔታ ከግምት በማስገባት፣ በግልጽ እና ፍትሐዊ መንገድ ምላሽ እንዲሰጥበት፣ ኢሰመጉ ጠይቋል።
የስልጤ ዞን አስተዳደር በበኩሉ፣ በቅበት ከተማ የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ የመብቶች ተሟጋች ተቋሙ ያወጣው መግለጫ፣ “ሐሰተኛ እና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው፤” ሲል ተቃውሞውን ገልጿል። ከቅበት ከተማ ተፈናቅለው በቡታጅራ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ከ1ሺሕ200 በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች፣ አሁንም በደብሩ እንደሚገኙና ከፍተኛ ችግር ላይ እንደወደቁ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል። ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።