ለመንግስት በኮንትራትነት ይሠራ የነበረ አብረሃም ተክሉ ለማ የተባለ ትውልደ ኢትዮጵያ የአሜሪካንን መንግስት በመሰለል ባለፈው ነሐሴ 18 ቀን 2015 በቁጥጥር ሥር መዋሉን ዛሬ ይፋ የሆነው የክስ ሰንድ አመልክቷል።
የኢንፍሮሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆነው፣ የሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሜሪላንድ ነዋሪው የ50 ዓመቱ አብረሃም ተክሉ ለማ፣ ሌላ ሀገርን ለመደገፍ የብሄራዊ መከላከያ መረጃን በማስተላለፍ፣ የብሄራዊ መከላከያ መረጃን ሌላ ሀገርን ለመደገፍ ለማስተላለፍ በማሴር እንዲሁም ሆን ብሎ የብሄራዊ መከላከያ መረጃን በግል መያዝ የሚሉ ክሶች ተመሥርተውበታል።
በቀረበው ክስ ላይ እንደተመለከተው፣ ከታህሳስ 2014 እስከ ነሐሴ 2015 ባለው ግዜ ውስጥ ግለሠቡ የስለላ ሪፖርቶችን ኮፒ በማድረግ፣ ሚስጥራዊ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምልክቶችን ሠርዟል ተብሏል። “ሚስጥር” እና “ከፍተኛ ሚስጥር” የሚሉ ምልክቶችን ጥበቃ ከሚደረግበት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ሆኖ መሠረዙን ክሱ አመልክቷል።
ሰንዶቹ አንድ ሀገርን ወይም አንድን አካባቢ የሚመለከቱ እንደሆኑ እና ተከሳሹ ካለ ፈቃድ ኮፒ ማድረጉ፣ ማስወገዱ እና በግል መያዙ ተመልክቷል።
አብረሃም ተክሉ ለማ ሚስጥራዊ የመከላከያ ሰነዶቹን የሌላ ሀገር መንግስት የስለላ ተቋም ጋር ግንኙነት ላለው ባለሥልጣን አሳልፎ መሥጠቱን ክሱ በተጨማሪ አመልክቷል። በመልዕክት ልውውጣቸውም ወቅት፣ አብረሃም ተክሉ ለማ ለባለሥልጣኑ መረጃን በማስተላለፍ መርዳት እንዳሚሻ ገልጿል ብሏል ክሱ።
አብረሃም ተክሉ ለማ ለውጪ ሀገር ባለሥልጣኑ አስተላልፎታል የተባለው መረጃ፣ በስም ባልተጠቀሰው ሀገር እና በቀጠናው የሚገኝን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ የሳተላይት ምስል እና ሌሎች ሌሎች ወታደራዊ መረጃዎችን ይጨምራል ተብሏል።
ሁለቱ የስለላ ክሶች እስከ ሞት ቅጣት ወይም እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እና ሰነዶችን ለግል መያዝ የሚለው ክስ ደግሞ እስከ 10 ዓመት የእስር ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችል ተመልክቷል።