የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ ማምሻውን አትላንታ ጆርጂያ በሚገኝ እስር ቤት እጃቸውን እንደሚሰጡ ሲጠበቅ፣ ደጋፊዎቻቸው በአቅራቢያው መሰባሰባቸው ታውቋል።
በእስር ቤቱ መግቢያ አካባቢ ፖሊሶች አጥር ሲሰሩ እና አካባቢውን ሲቃኙ ተስተውሏል።
ዶናልድ ትረምፕ በአትላንታ በሚገኝ ዘብጥያ ሪፖርት የሚያደርጉት፣ በጆርጂያ የ 2020ውን ፕሬዝደንታዊ መርጫ ውጤት ለመገልበጥ ሞክረዋል በሚል ክስ በመቅረቡ ነው። ለዶናልድ ትረምፕ አራተኛ ክስ መሆኑ ነው።
በእ.አ.አ ጥር 6 ቀን 2020 ዓ/ም በካፒቶል ላይ በተፈጸመው ጥቃት፣ ከፍተኛ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ወደ መኖሪያ ቤታቸው ወስደው በመደበቅ፣ እንዲሁም አንዲት የወሲብ ፊልም ተዋናይን ዝም ለማሰኘት ገንዘብ በመክፈል የሚሉት ሌሎቹ ክሶች ናቸው።
በአትላንታ ትረምፕ የእጅ አሻራ እንደሚሰጡ እና ፎቶግራፍ እንደሚነሱ ሲጠበቅ፣ ከዚህ በፊት በጠበቃቸው በኩል በተስማሙት መሰረት የ200 መቶ ሺሕ ዶላር ማስያዢያ እንደሚከፍሉም ይጠበቃል።
ከትረምፕ ጋር አብረው ከተከሰሱት አስራ ስምንቱ ውስጥ ዘጠኙ በትናንትናው ዕለት በእስር ቤቱ ቀርበው አሻራ መስጠታቸው እና ፎቶግራፍ መነሳታቸው ታውቋል።