በኬንያ ቲክቶክ ላይ የሚወጡ ቪዲዮች ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ከኩባንያው ጋር መስማማቷን ሀገሪቱ አስታወቀች፡፡
ስምምነቱ የተደረሰው “ቲክቶክ ያልተገቡ ቪዲዮዎችን ያሰራጫል” በሚል እንዲታገድ ከአንድ ግለሰብ ለሀገሪቱ ፓርላማ ከቀናት በፊት ጥያቄ መቅረቡን ተከትሎ ነው፡፡
ባይት ዳንስ በተሰኘው የቻይና ኩባንያ የሚተዳደረው ቲክቶክ፣ የግል መረጃ አያያዝን እና ደህንነትን በተመለከተ በመላው ዓለም ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል።
“የአጭር ቪዲዮ ማጋሪያው ኩባንያ ቲክቶክ፣ በመድረኩ ላይ የሚወጡትን ቪዲዮዎች መቆጣጠርን በተመለከተ ከኬንያ ጋር በጋራ ይሠራል” ሲል የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ጽ/ቤት አመልክቷል። ይህን በተመለከተም ከኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሾ ዚ ችው ጋር መነጋገራቸውን ቢሮው ጨምሮ አስታውቋል።
በስምምነቱ መሠረት፣ “ያልተገቡ ናቸው” የሚባሉ ቪዲዮች ከመድረኩ እንደሚወገዱ ታውቋል።
በአፍሪካ በቲክቶክ ላይ የሚወጡትን የቪዲዮዎች ይዘት በተመለከተ ቁጥጥር ለማድረግ ኩባንያው በኬንያ ቢሮ እንደሚከፍት ዋና ሥራ አስፈጽሚው ሾ ዚ ችው ይፋ ማድረጋቸውም ታውቋል።