በፕሪቶርያው ስምምነት ከእስር መፈታት ሲገባቸው ያልተፈቱ እስረኞች እንዳሉ ተገለጸ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል: የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ በተካሄደበት ወቅት ከወደሙ የጦር መሳሪያዎች አንዱ።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ በፕሪቶርያው ስምምነት ቢቋጭም፣ በጦርነቱ ወቅት፣ ከህወሓት ጋራ ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው ከታሰሩ የትግራይ ተወላጆች መካከል አሁንም ከእስር ያልተለቀቁ እንዳሉ፣ አንድ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀስ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ የቤተሰብ አባላት እና ክልሉ አስታወቀ።

በጦርነቱ ወቅት፣ በተለያዩ የዐማራ ክልል አካባቢዎች የታሰሩ ንጹሐን የትግራይ ተወላጆች እና ሕጋዊ የዳኝነት አካሔድን ባልተከተለ መንገድ ተከሠው የተፈረደባቸው የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በሰላም ስምምነቱ መሠረት መፈታት ሲገባቸው፣ አሁንም ድረስ ታስረው እንደሚገኙ ማረጋገጡን፣ ሂዩማን ራይትስ ፈርስት የተባለ ኢትዮጵያዊ የመብት ተሟጋች ድርጅት ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቀ።

እስረኞቹ፣ ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ በእስር ላይ መቆየት እንዳልነበረባቸው፣ ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩት የመብት ተሟጋቹ ድርጅት የሕግ ባለሞያ አቶ መብርሂ ብርሀነ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እስረኞቹን እንዲለቋቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ፣ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ካልተፈጸሙት ነገሮች አንዱ፣ የእስረኞች ፍቺን የሚመለከት ነው፡፡ ከፌዴራሉ መንግሥት ጋራ ሁሌም ውይይት ይደረግበታል፤ ብሏል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ፣ ከዐማራ ክልል መንግሥት፣ ከፌደራል ዐቃቤ ሕግ፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

Your browser doesn’t support HTML5

በፕሪቶርያው ስምምነት ከእስር መፈታት ሲገባቸው ያልተፈቱ እስረኞች እንዳሉ ተገለጸ

/በአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢዎች የተጠናቀረ ዘገባ ነው። የትግርኛ ክፍል ባልደረባ ገብረ ገብረመድኅን ከዘገባው አስተዋፅኦ አድርጓል።//