በዐማራ ክልል፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ደምቢያ ወረዳ በጯኺት ከተማ አካባቢ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና በ"ፋኖ" ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት፣ ሲቪሎችን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች እንደተገደሉ፣ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ምክር ቤት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት፣ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ከፍተኛ አመራሮች፣ በጎርጎራ ከተማ እየተገነባ ያለውን "ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት ለመጎብኘት በጉዞ ላይ እያሉ፣ በታጠቁ ኀይሎች ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው አስታውቋል።
“ጉዳዩን በውል ያልተረዱ የታጠቁ ኃይሎች ናቸው፤” ሲል፣ የወረዳው አስተዳደር በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ መንገድ በመዝጋታቸውና ትንኮሳ በማድረጋቸው በተከተለው ግጭት፣ የሰው ሕይወት እንዳለፈና የአካል ጉዳትም እንደ ደረሰ ገልጿል።
ምክር ቤቱ፣ በግጭቱ የሞቱትንም ኾነ የቆሰሉትን ሰዎች በቁጥር አላስቀመጠም። የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው፣ በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱና ራሳቸውን "ፋኖ" ብለው የሚጠሩ ግለሰቦች፣ በግጭቱ ምክንያት፣ ሰላማውያን ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።
"የዐማራ ሕዝብ ጥያቄ አልተመለሰም፤" በሚል፣ በአኹኑ ሰዓት፣ በአካባቢው “ፋኖ” በሚል አደረጃጀት ታጥቀው እንደሚንቀሳቀሱ የገለጹልን አቶ ሙሉጌታ የተባሉ ግለሰብ፣ ግጭቱ የተቀሰቀሰው፥ ገዳም በሚገኝበት አካባቢ፣ "ገበታ ለሀገር" በሚባለው ፕሮጀክት ውስጥ፣ በጾም ቀን ከብት በመታረዱ፣ የአካባቢው ሰው ተቃውሞ በማሰማቱ እንደኾነ ተናግረዋል።
በዚኹ ደም አፋሳሽ ግጭት ምክንያት፣ ከጎንደር ከተማ ወደ ጎርጎራ የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ እንደነበርም፣ አቶ ሙሉጌታ አመልክተዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ከአካባቢው እና ከክልል ባለሰልጣት ለማግኘት በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ስልኩ ባለመነሳቱ ምክንያት ማካተት አልቻልንም።
/የዘገባውን ሙሉ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/