የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች የግልጽነት ችግር ለመንግሥት አካላት የቁጥጥር ሥርዐት አደገኛ አዝማሚያ እንደኾነ ባለሞያዎች ተናገሩ

Your browser doesn’t support HTML5

በኢትዮጵያ የገዢው ፓርቲ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ለአገሪቱ ለውጥ እና ብልጽግና ተግባራዊ ማሳያዎች ይኾናሉ፤ ያሏቸውንና በግንባር ቀደምነት የሚመሯቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ ከፍጻሜ በማድረስ የምረቃቸውን ሪባን እያከታተሉ ሲቆርጡ ይታያሉ፡፡

በተለያዩ የገበታ ስያሜዎች በሚሊዮኖች ፈንድ የሚሰበሰብባቸውና ፈሰስ የሚደረግባቸው እኒኽ ፕሮጀክቶች፣ “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጪነት” እየተባሉ ሲከናወኑና ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት እየተደረጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን፣ ከሕግ አውጪው ምክር ቤት እና ከቁጥጥር አካሉ ተደራሽነት ውጭ ናቸው፤ በሚል፥ የሙዓለ ንዋዩ ምንጭ፣ የአጠቃቀሙ ግልጽነት እና የተጠያቂነቱ አግባብ፣ እንዲሁም ከአገሪቱ ተጨባጭ ኹኔታ አኳያ ያላቸው አንገብጋቢነት፣ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እያጫሩ ይገኛሉ፡፡

ጥያቄዎቹ፣ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ከመስኩ ምሁራን አልፎ የአገሪቱ የመጨረሻው መንግሥታዊ አካል በኾነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድም ሁለት ጊዜ ቢነሣም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከባለሥልጣኖቻቸው የተሰጡ ምላሾች፣ አጥጋቢ እንዳልኾኑ ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡

የወርኀ መጋቢት 2010 ዓ.ም. የሥርዐተ መንግሥት ለውጥ ተከትሎ በተቆጠሩት አምስት ዓመታት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቅርብ ክትትል በልዩ ልዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፥ በቢሊዮን ብሮች ወጪ የተደረገባቸው ዐዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተሠሩ ለአገልግሎት ክፍት እየኾኑ ይገኛሉ፡፡

በመዲናዪቱ ዐዲስ አበባ፣ እንጦጦን አካሎ የሱሉልታ ግርጌን ይዞ ጣፎ የሚደርሰውና የ“ጫካ ፕሮጀክት” እየተባለ የሚጠራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግማሽ ትሪሊዮን ብር የቤተ መንግሥት ፕሮጀክት፣ የቅርቡ እና በሰፊው እያነጋገረ ያለው ነው፡፡

ግንባታቸው የተጠናቀቁትና አሁንም በግንባታ ላይ ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የፋይናንስ ምንጭ እና የአጠቃቀም ግልጽነት አስመልክቶ፣ በግልጽ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ፣ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ከመስኩ ምሁራን አልፎ የአገሪቱ የመጨረሻው ሕግ አውጪ አካል በኾነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች፣ ተደጋጋሚ ጥያቄን እያስነሣ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የአገሪቱን የቀጣይ ዓመት በጀት ለማጽደቅ በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ ላይ ተገኝተው ምላሽ ከሰጡባቸው የእንደራሴዎቹ ጥያቄዎች ውስጥ፣ የፕሮጀክቶቹ የገንዘብ ምንጭ እና የአጠቃቀማቸውን ግልጽነት የተመለከተው ይገኝበታል፡፡

የፕሮጀክቶቹ የፋይናንስ ምንጭ፣ በእርሳቸው ጠያቂነት በልግስና የተገኘ ገንዘብ በመኾኑ፣ በአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ውስጥ እንደማይካተትና ፓርላማውም ጥያቄ ሊያነሣበት እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምክር ቤቱን ሊያሳስቡት ይገባል ያሏቸውን ሌሎች መጠይቆች ማንሣትን መርጠዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶክተር አክሎግ ቢራራ እንደሚሉት፣ እንደ ኢትዮጵያ የካፒታል እጥረት ያለባቸው ሀገራት፣ ፋይናንስን፥ በግልጽነት እና ሓላፊነት በተሞላበት መልኩ የማስተዳደር መርሕን ሊከተሉ ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በማንኛውም መልኩ የሚያገኙት ገንዘብ፣ የሥራ አስፈጻሚው አካል ቁንጮ ኾነው አገርን በሚመሩበት የርእሰ መንግሥት ሥልጣናቸው እስከ ኾነ ድረስ፣ ሕጋዊ የበጀት ዝግጅትን ተከትሎ ሊሠራበት እንደሚገባ፣ ባለሞያው ዶር. አክሎግ ያስረዳሉ፡፡

በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመምህርነት ያገለገሉት፣ የሕገ መንግሥታዊ ሕግ እና መንግሥታዊ አስተዳደር ምሁር አቶ እንዳልካቸው ገረመው፣ መንግሥታዊ ወጪዎች፣ በማንኛውም መልኩ ሕጋዊ መሠረት ያስፈልጋቸዋል፤ ይላሉ፡፡

ለዚኽም፣ ጥቅም ላይ የሚውሉ ወጪዎች፣ ለሕግ አውጪው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መጽደቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የትኛውም የመንግሥት አካል፣ ሕጉንና

አሠራሩን ጠብቆ ገንዘቡን ወጪ ስለማድረጉ፣ በሚመለከተው አካል ለመቆጣጠር ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥር ያመለክታሉ፡፡

ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሔደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጉዳዩ በድጋሚ የተነሣላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በዐዲስ አበባ የተገነቡ ፓርኮች የገንዘብ ምንጭ፣ ከቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተገኘ ድጋፍ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ሥራው ራሳቸው በመረጡት ተቋራጭ የተሠራ በመኾኑ፣ ኦዲት ማድረግ ከተፈለገ፣ ድጋፉን የሰጡትን የሚመለከት ነው፤ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዚኽ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የማይስማሙት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶክተር አክሎግ ቢራራ፣ ዶር. ዐቢይ በማንኛውም መልኩ የሚያገኙት ፋይናንስ፣ ሀገርን በወከሉበት ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚነት ሥልጣናቸው እስከኾነ ድረስ፣ በሕጋዊ የበጀት አሠራር አልፎ ከጥቅም ላይ ሊውል እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

የሕገ መንግሥታዊ ሕግ እና መንግሥታዊ አስተዳደር ምሁሩ አቶ እንዳልካቸው ነጋሽ፣ እንዲኽ ዐይነት ወጪዎችን አስመልክቶ፣ ግልጽነት ያለው አሠራር አለመኖሩና የሕዝብ ተወካዮች ላነሧቸው ጥያቄዎች፣ ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጡ ምላሾች፣ በመንግሥት አካላት የቁጥጥር ሥርዐት ላይ ችግር የሚፈጥር አደገኛ አዝማሚያ እንደኾነ ያሳስባሉ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቅርብ ክትትል፣ በዐዲስ አበባ የተሠሩ የአንድነት፣ የእንጦጦ፣ የወዳጅነት ቁጥር እና ሁለት ፓርኮች፣ እንዲሁም የሐላላ ኬላ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የሳይንስ እና ዕፀዋት ሙዝየሞች እና የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ተጠናቅቀው፣ ለሕዝብ ጉብኝት እና ግልጋሎት ክፍት ኾነዋል፡፡

በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ካሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዳንዶቹ የተጠናቀቁ ሲኾን፣ እስከ ግማሽ ትሪሊዮን ድረስ ግዙፍ ወጪ ይጠይቃል የተባለውን “የጫካ ፕሮጀክት” የቤተ መንግሥት ግንባታ ጨምሮ፣ ዐዲስ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ግንባታዎችም እንደቀጠሉ ይገኛሉ፡፡

በፕሮጀክቶቹ የፋይናንስ ምንጭ፣ የአጠቃቀም ግልጽነት፣ የተጠያቂነት አግባብ እና አንገብጋቢነት ላይ የሚነሡ ጥያቄዎች፣ አሁንም ቀጥለዋል፡፡

/የዘገባውን ሙሉ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/