ካንሰርን ለማከም የሚውል መሣሪያ መፈጠሩ እና የተመራማሪዎች ተስፋ

Your browser doesn’t support HTML5

በሎስ አንጀለስ የሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ ለካንሰር ሕክምና ሲያገለግል የቆየውን ኬሞቴራፒ፣ ወደፊት ለመተካት የሚችል አማራጭ መሣሪያ ፈጥረዋል።

ሰውነት፣ በተፈጥሮ ያለውን በሽታን የመዋጋት ዐቅም በመጠቀም የሚሰጠው ሕክምና መሻሻል ሲያሳይ፣ አንድ ቀን ካንሰርን በውጤታማነት ማከም እንደሚቻል፣ የባዮኤንጂነር ባለሞያ እና የመሣሪያው ተባባሪ ፈጣሪ የኾነችው ኔግን ሞጀዲ ጠንካራ ተስፋ አላት፡፡

“በሰውነት ውስጥ በሽታን የሚዋጉ ሴሎችን በመጠቀም እና ሰውነት በተፈጥሮ ያለውን የካንሰር እባጭን የማሰወገድ ዐቅም በመጠቀም፣ የካንሰር ሴሎቹን ማስወገድ ይቻላል፤” የምትለው ሞጀዲ፣ “ይህ ለእኔ በጣም አስደሳች ነገር ነው፤” ብላለች።

የኢራን ተወላጇ ሞጀዲ እና ባዮኤንጂነሩ ባለቤቷ ማህዲ ሃሳኒ፣ በሎስ ኤንጀለስ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሕክምና እና ከኤንጂነሪንግ መስክ የተውጣጡ አባላት ያሉበት የምርምር ቡድን አካል ናቸው። የምርምር ቡድኑ “ሲምፍኖድ” ብለው የጠሩትን የእርሳስ ላጲስ የሚያኽል፣ ስፖንጅ መሰል የኾነና በራሱ ፈራርሶ ሊጠፋ የሚችል መሣሪያ ሠርተዋል።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፣ መሣሪያው በካንሰር እባጭ ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። ከዚያም፣ ሰውነት በራሱ ከሚከላከልበት ዐቅም የተሻለ ቅስም(ኀይል/ጉልበት) ያለውን መድኃኒት ይረጫል።

“ይህም፣ ልክ በአቅራቢያ እንደሚገኝ የሰውነት ማሠልጠኛ የስፖርት ጂም ነው። ሴሎቹን ሰብስቦ ያሠለጥናቸዋል። ከመሣሪያው ሲወጡም፣ የካንሰር እባጩን ለመዋጋት ዝግጁ ይኾናሉ፤” ሲሉ፣ ተባባሪው ፈጣሪው እና የሞጀዲ ባለቤት ማህዲ ሓሳኒ በተጨማሪ አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኢሚዩኖሎጂ ፕሮፌሰር እና ሞጀዲን በጥናቷ የሚያማክሩት ማኒሽ ቢዩት እንደሚሉት፣ ሐሳቡ፥ ካንሰርን የሚዋጉት ወይም የካንሰርን ሴሎች የሚገድሉት ‘ቲ ሴሎች’ ሥራቸውን እንዳይሠሩ የሚያደርጉትና “የቁጥጥር” የሥራ ድርሻ ያላቸውን ሌሎች ‘ቲ ሴሎች’ ማገድ ነው።

“ይህም ሰውነት፣ በተፈጥሮ ባለው በሽታን የመከላከል ዐቅም፣ ሁሉንም የካንሰር ዐይነቶች እንዲዋጋ ኹኔታዎችን ያመቻቻል። የጡት ካንሰርን ብቻ ሳይኾን፣ ሁሉንም ዐይነት የካንሰር እባጮችን ለመዋጋት” ሲሉ፣ ሓሳኒ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

አጥኚዎቹ የሠሩትና “ሲምፍኖድ” የተሰኘው መሣሪያ፣ የጡት ካንሰር ባለባቸው አይጦች ላይ ተሞክሮ፣ 80 በመቶ በሚኾኑት ላይ የካንሰሩን እባጭ ቀንሷል። የካንሰሩን ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል መሠራጨቱን ደግሞ መቶ በመቶ አስቁሟል።

አጥኚዎቹ፣ በሰው ላይ የሚያደርጉትን ሙከራ፣ በመጪው የፈረንጆች 2024 ለመጀመር ተስፋ ያደርጋሉ። ቴክኖሎጂው፣ በተቻለ ፍጥነት ካንሰርን ለማከም እንዲውልም ያልማሉ።