ፍርድ ቤቱ የሽብር ወንጀል ተከሣሾችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አደረገ

Your browser doesn’t support HTML5

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ዛሬ ባዋለው ችሎት፣ በሽብር ወንጀል የተከሠሡ እስረኞች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡

የዋስትናው ጥያቄ ውድቅ የኾነበት ብይን ከተነበበ በኋላ፣ ተከሣሾች በቅጽበት በደማቅ ጭብጨባ የታገዘ መፈክር አሰምተዋል፡፡

የዋስትና ጥያቄውን፣ በሙሉ ድምፅ ውድቅ ያደረገው ችሎቱ፣ የተከሣሽ ጠበቆችን የክሥ መቃወሚያ ለማድመጥ፣ ለሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ባዋለው ችሎት፣ አራት የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎችን ጨምሮ በ24 የሽብር ወንጀል ተከሣሾች በቀረበው የዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡

ችሎቱ የዛሬውን ብይን የሰጠው፣ ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከሣሽ ጠበቆች እና በዐቃቤ ሕግ መካከል የተደረገውን የዋስትና ክርክር መነሻ በማድረግ ነው፡፡

በወቅቱ በተደረገው ክርክር፣ በተከሣሽ ጠበቆች እና በዐቃቤ ሕግ በኩል የነበረውን ሙግት ችሎቱ በንባብ ሲያሰማ፣ ጠበቆች፥ ደንበኞቻቸው የተከሠሡት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በወጣው ዐዋጅ መሠረት በመኾኑ፣ የዋስትና ጉዳያቸው፣ በሽብር ወንጀል ዐዋጅ እንዲታይና ይህ ዐዋጅ ደግሞ ዋስትና እንደማያስከለክል በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በክሡ ያቀረበው የወንጀል ፍሬ ነገርም ዋስትና አያስከለክልም፤ ያሉት ጠበቆቹ፣ ደንበኞቻቸው ቋሚ አድራሻ እና ሥራ ያላቸው፣ የቤተሰብ ሓላፊም እንደኾኑ ጠቅሶ፣ በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ውጪ ኾነው እንዲከታተሉ ጠይቀው ነበር፡፡

በተጨማሪም፣ አራቱ የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች፡- መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ እና ገነት አስማማው፣ የቀረበባቸውን ክሥ፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ በኩል ሠርተውታል በተባለ ሥራ ምክንያት በመኾኑ፣ ጉዳያቸውም በብዙኃን መገናኛ ዐዋጁ መሠረት ሊታይ እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ተከሣሾቹ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት የተከሠሡ እንደኾኑና ፈጽመዋል በተባለው የሽብር ወንጀል፣ የ217 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ በዚኽም ብዙዎቹ እንደተጎዱና ከፍተኛ ንብረትም እንደወደመ፣ ይህም፣ ከ15 ዓመት በላይ እንደሚያስቀጣ ጠቅሶ፣ የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል፡፡

የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎቹም፣ የተከሠሡት፣ በሽብር ወንጀል እንጂ በጋዜጠኝነት ሥራቸው አይደለም፤ በማለት ተከራክሯል፡፡

የሁለቱን የግራ ቀኝ ክርክር መመርመሩን የገለጸው ችሎቱ፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣው ዐዋጅ፣ ስለ ዋስትና ጉዳይ የደነገገው ነገር ባይኖርም፣ በዐዋጁ ያልተጠቀሱ ጉዳዮች፣ በመደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዐት ሕግ እንደሚታዩ፣ እንዲሁም የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎቹ የተከሠሡት በሽብር ወንጀል እንደኾነ በማስረዳት፣ የተከሣሽ ጠበቆችን መከራከሪያ ውድቅ እንዳደረገው አስታውቋል፡፡

የዋስትናው ጉዳይ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዐቱ ቢታይ እንኳን፣ ዋስትና ሊከለከሉ እንደማይገባ ጠበቆች ሲከራከሩ፣ ዐቃቤ ሕግ ደግሞ፣ ዋስትና አይገባቸውም ያለበትን ነጥቦች አስረድተዋል፡፡ ከተከሣሽ ጠበቆች መካከል አንዱ የኾነው፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛከኝ፣ ስለ ክርክሩ ይዘት እና ስለ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አብራርተዋል፡፡

የዋስትና ጥያቄውን በሙሉ ድምፅ ውድቅ አድርጎ፣ ተከሣሾቹ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ኾነው እንዲከታተሉ የወሰነው ችሎቱ፣ ለሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የችሎቱ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ፣ በችሎቱ የነበሩ ተከሣሾች፣ በቅጽበት ከመቀመጫቸው ተነሥተው በደማቅ ጭብጨባ የታገዘ መፈክር አሰምተዋል፡፡ በመፈክራቸውም፣ “የታሰርነው በማንነታችን ነው፤” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ችሎቱን ለመከታተል የታደሙ የተከሣሽ ቤተሰቦች፣ ወዳጆቻቸው እና ሌሎች ታዳሚዎችም፣ ደማቅ ጭብጨባ በማድረግ አጋርነታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡

ከችሎቱ ከወጡም በኋላ ጭብጨባቸውንና መፈክራቸውን ያላቋረጡት ተከሣሾቹ፣ በተዘጋጁላቸው ተሸከርካሪዎች ወደ እስር ቤት በማምራት ላይ እያሉ፣ በጋራ መዝሙር ሲያሰሙም እንደ ነበር ተመልክተናል፡፡ ቤተሰቦቻቸው እና ሌሎች የችሎት ተመላልካቾችም፣ በከፍተኛ ጭብጨባ እና በማጽናኛ ቃላት ሲሸኟቸው ታይተዋል፡፡ የተደበላለቀ ስሜት በተንጸባረቀበት በዛሬው ኹነት፣ የመስከረም አበራን እናት እና እህቷን ጨምሮ በግልጽ ሲያነቡ የነበሩ የሌሎች ተከሣሾች የቤተሰብ አባላትንም ተመልክተናል፡፡

በክሥ መዝገቡ ላይ ከተጠቀሱ 51 የሽብር ወንጀል ተከሣሾች መካከል፣ ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ የሚገኙ 27 ተከሣሾችን፣ ዐቃቤ ሕግ ከፌዴራል ፖሊስ ጋራ በመኾን፣ በመጥሪያ እንዲያቀርብም ችሎቱ በዛሬ ውሎው ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡