በፓትርያርኩ የተመራ የሰላም ልኡክ በመቐለ ጉብኝት በማድረግ የ20 ሚሊየን ብር ሰብአዊ ርዳታ ለገሰ

Your browser doesn’t support HTML5

በፓትርያርኩ የተመራ የሰላም ልኡክ በመቐለ ጉብኝት በማድረግ የ20 ሚሊየን ብር ሰብአዊ ርዳታ ለገሰ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ የሚመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ልዑክ፣ ዛሬ ጠዋት መቐለ ገብቷል፡፡

በቅዱስነታቸው ለተመራው የሰላም ልኡክ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት አቀባበል ቢያደርግም፣ የትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት እና የሥራ ሓላፊዎች ግን በሥነ ሥርዐቱ ላይ አልተገኙም፤ ከፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው ረዳ ጋራ በፕላኔት ሆቴል በተደረገው አጭር ውይይትም ላይ አልተሳተፉም፡፡

የትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ባለመገኘታቸው ማዘናቸውን ያልሸሸጉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ “ልዩነት በውይይት ነው የሚፈታው፤ ብፁዓን አባቶች ቢገኙ መልካም ነበር፤” ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳም፣ ልዩነት በውይይት መፈታት ኣለበት ብለው እንደሚያምኑና የትግራይ ክልል አባቶች ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥረት እንደሚያደርጉ፣ ኾኖም ሊያስገድዷቸው እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለክልሉ ተጎጂዎች እንዲውል የለገሰውን የ20 ሚልዮን ብር ሰብአዊ ርዳታ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አስረክበዋል፤ ልኡካኑ ተፈናቃዮችም ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

SEE ALSO: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ ጠየቀች

፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተሠየሙ ስድስት የሰላም ኮሚቴ አባላት ከኾኑ ሊቃነ ጳጳሳት እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋራ፣ ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠሩ ቅሬታዎች እና ጥያቄዎች ላይ ለመወያየት እና ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ መቐለ ከተማ ገብተዋል፡፡

ለሰላም ልኡካኑ በተደረገው የአቀባበል ሥነ ሥርዐት ላይ፣ በክልሉ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የሥራ ሓላፊዎች እንደሚገኙ በወጣው መርሐ ግብር ተጠቁሞ የነበረ ቢኾንም አልተሳተፉም፤ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋራ በፕላኔት ሆቴል በተካሔደው አጭር ውይይትም ላይ አልተገኙም፡፡

ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በጦርነቱ በክልሉ ሕዝብ ላይ የደረሰውን በደል እንዲሚረዱ ተናግረው፣ በጉዳዩ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፈው ሳምንት ይቅርታ መጠየቁን አስታውሰዋል፡፡ ከክልሉ አህጉረ ስብከት አባቶች ጋራ ተቀምጠን ብንወያይ መልካም ነበር፤ ብለዋል ቅዱስ ፓትርያርኩ፡፡

“ያለፈው መከራ እና እልቂት ይበቃናል፤” ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ሰላሙ እንዲቀጥል ጸሎታችንና ምኞታችን ነው፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡በትግራይ ክልል ካሉ አባቶች ጋራ ያለው ልዩነት በውይይት እንዲፈታ ጥረቱ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ለክልሉ ተጎጂዎች እንዲደርስ የወሰነችውን የ20 ሚልዮን ብር ሰብአዊ ርዳታ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ተረክበዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው፣ የተደረገው ድጋፍ ቢዘገይም የሚመሰገን ነው፤ ብለዋል::

ልዩነት በውይይት መፈታት ኣለበት ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የትግራይ ክልል አባቶች ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ ኾኖም ለማስገደድ ፍላጎት የለኝም፤ በማለት ተናግረዋል፡፡

የሰላም ልኡካኑ፣ በተፈናቃዮች ማእከል ጉብኝት ያደረጉ ሲኾን፣ ቅዱስነታቸው፣ የማጽናኛ ትምህርት እና አባታዊ ቡራኬም ሰጥተዋል፡፡ ተፈናቃዮቹም፥ “ድምፅ አልኾናችኹንም” በማለት እና “ጦርነቱን ደግፋችኋል” በማለት፣ በድምፅ እና በባነር ላይ በሠፈሩ ጽሑፎች ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

“እንኳን የልባችኹን ተናገራችኹ፤” ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩም፣ ወደ ቀዬአችኹ እንድትመለሱ ለሚመለከተው እናሳውቀለን፤ ብለዋል፡፡