ማመጣጠንን የሚሻው የኢትዮጵያውያን ምግብ

Your browser doesn’t support HTML5

ማመጣጠንን የሚሻው የኢትዮጵያውያን ምግብ

"ልሔም የሥነ ምግብ ማማከር አገልግሎት"፥ በሥነ ምግብ ባለሞያዋ ወጣት፣ ቤተ ልሔም ላቀው የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡ቤተልሔም፣ ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ በምግብ ሳይንስ እና በተግባራዊ አመጋገብ ተመርቃለች፡፡ ቤተ ልሔም፣ ለሕፃናት አልሚ ብስኩት የሚያመርተው "የቤኑ ፉድስ" ፋብሪካም አጋር መሥራች ናት፡፡

"ልሔም" በተሰኘው የሥነ ምግብ ተቋሟ አማካይነትም፣ ሕፃናትን፣ እናቶችንና የተለያዩ ሥር የሰደዱ ሕመሞች ያሉባቸውን ሰዎች የማማከር አገልግሎት በመስጠት፣ ሰዎች ወደ ጤናማ አመጋገብ እና አኗኗር እንዲመጡ ታግዛለች፡፡

ቤተልሔም፣ የሥነ ምግብ አገልግሎት ሲባል፣ ብዙውን ጊዜ እውቀቱ እና ክህሎቱ የሚቀሰመው በፈረንጅ ምግቦች በመኾኑ፣ በብዙዎች ዘንድ፣ ለተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍል ብቻ የተተወ ይመስላቸዋል፤ ትላለች፡፡

ይኹን እንጂ፣ የኢትዮጵያውያን ምግብ፣ ለጤናማ አመጋገብ የተመቸ እና ማመጣጠንን ብቻ የሚሻ ነው፤ ትላለች፡፡ ሰዎች ሊገነዘቡት የሚገባው ሌላው ነገር፣ አመጋገብ፥ እንደ ግለሰቡ የጤና ኹኔታ መቃኘት እንዳለበት በአጽንዖት ታሳስባለች፡፡ ይህን መሰል የጤና ምክሮችን፣ "ልሔም ኑትሪሽን" የተሰኘውን የዩቱብ ገጽ እና ልዩ ልዪ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ታስተላልፋለች፡፡

ቤተ ልሔም ላቀው፣ በተቋሙ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም በጤናማ አመጋገብ ላይ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ ቆይታ አድርጋለች፡