የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎቹ የሦስት ቀናት የረኀብ አድማ አደረጉ

Your browser doesn’t support HTML5

የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎቹ የሦስት ቀናት የረኀብ አድማ አደረጉ

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች፣ የሦስት ቀናት የረኀብ አድማ እያደረጉ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡ በኅቡእ ተደራጅቶ መንግሥታዊ ሥልጣንን በኃይል ከመያዝ የተቀናጀ የሽብር ተግባራት ጋራ በተያያዘ የወንጀል ክሥ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት በመከታተል ላይ የሚገኙት በቁጥር 47 የሚደርሱት ተጠርጣሪዎቹ፣ በረኀብ አድማ ላይ መኾናቸውን፣ ጠበቆቻቸው እና የቤተሰብ አባላት፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

የረኀብ አድማውን ያደረጉበት ዋና ምክንያት፣ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋራ በተያያዘ፣ በዐማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ነው፤ ያሉት እስር እንዲቆም ለመጠየቅ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ በበኩሉ፣ የረኀብ አድማ እንዳልተደረገና ምግብ እየገባላቸው እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ምሁራንና የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎችን ጨምሮ፣ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙና ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት በመከታተል ላይ የሚገኙ 47 የሚደርሱ ግለሰቦች፣ ካለፈው ሰኞ፣ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በረኀብ አድማ ላይ እንደሚገኙ፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ የኾኑት፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ “በዐማራ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን በማፍረስ ክልላዊ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ በኅቡእ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች” ሲል የገለጻቸው ተከሣሾች፣ እንዲሁም የሚዲያ እና ፕሮፓጋንዳ ክንፍ ትመራለች ያላት “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዩቲዩብ ብዙኃን መገናኛ አዘጋጅ እና ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በመስጠት የምትታወቀው መስከረም አበራ፣ በረኀብ አድማ ላይ ከሚገኙት የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች መካከል አንዷ ነች፡፡ ባለቤቷ ፍጹም ገብረ ሚካኤል፣ ስለ አድማው አስተያየት ሰጥቶናል፡፡

የረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቼው ቤተሰብ አባል የኾነው አቶ ሲሳይ አብርሃምም እንዲሁ፣ ከሰኞ ጀምሮ ምግብ እንዳላደረሱላቸው ነግረውናል፡፡የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ አቶ ጄላን አብዲ በበኩላቸው፣ በተጠርጣሪዎቹ የረኀብ አድማ አልተደረገም፤ ምግብም እየቀረበ ነው፤ ብለዋል፡፡ ይህንም ከወንጀል ምርመራ ቢሮ ማጣራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠበቃ ሰሎሞን ገዛኸኝ በበኩላቸው፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ፣ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎችን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሔደው ማናገራቸውንና የረኀብ አድማው መቀጠሉን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል፡፡ያም ኾነ ይህ፣ ከሰኞ ጀምሮ በረኀብ አድማ ላይ ይገኛሉ የተባሉት፣ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች፣ ለሦስት ቀናት የሚያደርጉት የረኀብ አድማ፣ በዛሬው ዕለት እንደሚያበቃ ታውቋል፡፡

የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ በኅቡእ አደረጃጀት ውስጥ ሲንቀሳቀሱና የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 47 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለጸው፣ ባለፈው ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በአወጣው መግለጫ ነበር፡፡ ተጠርጣሪዎቹ፣ የዐማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን የግድያ ዒላማ በማድረግ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ የክልሉን መንግሥታዊ መዋቅር በመቆጣጠር፣ የፌደራል መንግሥትን ለመጣል በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ተደራጅተውና ተቀናጅተው በኅቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበር፤ ብሏል፡፡

በቁጥጥር ሥር ከሚገኙት ተጠርጣሪዎች መካከል የሚበዙት፣ ሁከት እና ብጥብጥ በመፍጠር ወንጀል ተጠርጥረው፣ ጉዳያቸውን ለአንድ ወር እና ከዚያ በላይ ሲከታተሉ ቆይተው፣ በሽብር ወንጀል ዐዲስ የክሥ መዝገብ የተከፈተባቸው ናቸው፡፡