በዛሬው የሴቶች ፕሮግራም መሰናዶአችን፥ አሳዳጊ አልባ ኾነው ተጥለው የተገኙ ጨቅላ ሕፃናትን ሰብስቦ በማሳደግ እና የቀን ሥራ እየሠሩ ኑሯቸውን ለሚገፉ እናቶች ጨቅላ ልጆች፣ የሕፃናት መቆያ አገልግሎት እየሰጠ በመከባከብ ላይ ስለሚገኝ የበጎ አድራጎት ማዕከል እናስቃኛችኋለን፡፡
በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው “ግሬስ” የተባለ ገባሬ ሠናይ ድርጅት፣ ከ800 በላይ ሕፃናትን ይዟል፡፡ ከእነዚኽም፣ ከ500 በላይ የሚኾኑቱ ሕፃናት፣ ወላጆቻቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት ያጡ ሲኾኑ፣ ቀሪዎቹ ጨቅሎች ደግሞ፣ እናቶቻቸው በቀን ሥራ ላይ በመሠማራታቸው አብረዋቸው የማይውሉ ናቸው፡፡
ከቀን ሠራተኛ እናቶች መሀከል የኾነችው እና ማየት የተሳናት የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ገነት አየለ፣ “ ግሬስ” የተሰኘው ገባሬ ሠናይ ማዕከል ባይኖር ኖሮ፣ ከእነልጇ ኑሮዋ ጎዳና ላይ መዋል ማደር እንደነበር ትናገራለች፡፡
ማዕከሉ ለአሳዳጊ አልባ ሕፃናት ድጋፍ ማድረግ ዋና ዓላማው መኾኑን ያስታወቁት ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ወርቁ ሐሳብ፣ ከሙዓለ ሕፃናት አገልግሎቱ ጎን ለጎን የተጠፋፉ ወላጆችን ማገናኘት፤ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን ማመቻቸት፤ ለችግረኛ ወላጆች የሥራ መወጠኛ ገንዘብ መስጠት እና የመሳሰሉትንም ድጋፎችን እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
“ግሬስ ማዕከል” የተሰኘው ግብረ ሠናይ ድርጅት፣ በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 13፣ በተለምዶ ገጠር መንገድ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ይገኛል፡፡ በአማሪካዊቷ ሜርሲ ሜሪክሰን እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1999 ዓ.ም. እንደተቋቋመ ይነገራል፡፡ ይኸው ማዕከል፣ አሳዳጊ አልባ ኾነው ተጥለው የሚገኙ ጨቅላ ሕፃናትን ሰብስቦ ማሳደግ፤ ነፃ የሕፃናት መዋያ አገልግሎት መስጠት፤ ከወላጆቻቸው ጋራ የተጠፋፉ ሕፃናትን ማገናኘት፤ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ማመቻቸት፤ ለችግረኛ ወላጆች የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ መስጠትንና መሰል ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ከዚኽ ጎን ለጎን፣ ነፃ የትምህርት እና የጤና አገልግሎትም ይሰጣል፡፡
ወደ ማዕከሉ፣ ጠዋት ጠዋት ጨቅላ ልጆቻቸውን አዝለው ከሚመጡ እናቶች መሀከል ማየት የተሳናት እና የ11ኛ ክፍል ተማሪ እንደኾነች የነገረችን ገነት በየነ አንዷ ናት፡፡ ገነት ለትምህርት፣ ከሰሜን ወሎ መቄት ወረዳ ወደ ባሕር ዳር እንደመጣች ነግራናለች፡፡ በከተማው ቤት ተከራይታ እየተማረችም ነበር፤ “እኔ ቤት ኪራዩን እከፍልልሻለኹ፤” ብሎ ቃል እንደገባላት የምትጠቅሰው ግለሰብ ግን፣ ሰብአዊ ኀዘኔታውን ለጾታዊ
ብዝበዛ ተጠቅሞ እብስ ማለቱንና እርሷም፣ ባላሰበችውና ባልተዘጋጀችበት እርግዝና ሳቢያ ለአስከፊ ችግር ተዳርጋ እንደነበር አውስታለች፡፡
በዚኹ፣ በ“ግሬስ” የሕፃናት መኖሪያ እና ማቆያ ገባሬ ሠናይ ማዕከል ያገኘናት ሌላዋ ወላጅ እናት፣ መዲና ኢብራሂም ናት፡፡ መዲና ተወልዳ ከአደገችበት ከቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅላ፣ ወደ ባሕር ዳር የመጣችው፣ በ12 ዓመቷ ወላጆቿ በመደራቸው ምክንያት እንደኾነ ታስረዳለች፡፡ ከባድ የጤና እክል እንደነበረባት የገለጸችው መዲና፣ ሕመሟን ተቋቁማ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ስትሠራ እንደነበር ታወሳለች፡፡ ኋላም የጀበና ቡና በማፍላት እና በመሸጥ ስትተዳደር ቆይታለች፡፡ ይህንኑ ሥራ በመሥራት ላይ ሳለች ከተዋወቀችው ሰው ጋራ ትዳር መሥርታ ለጥቂት ጊዜያት አብረው ቢቆዩም፣ ወዲያው በፍቺ እንደተለያዩ ትናገራለች፡፡ እንደተለያየች በወቅቱ ለመለየት ባልቻለችው እርግዝና፣ ሦስት መንታ ልጆችን ተገላግላለች፡፡
የ“ግሬስ” ማዕከል ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቁ ሐሳብ፣ ማዕከሉ በ13 ዓመታት ቆይታው፣ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሠርቷል፤ ይላሉ፡፡ በተለይ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት፣ 93 ሕፃናትን የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲያገኙ አድርጓል፤ አሳዳጊ ለማግኘት ዕድሜያቸው ያልፈቀደውንም ያሳድጋል። ከዚኽ ጋራ በተያያዘ ማዕከሉ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በነፃ እንደሚሰጥ አቶ ወርቁ ያብራራሉ።
በአካውንቲግ ዲግሪ ብትመረቅም፣ በአኹኑ ወቅት መተዳደሪያዋ ያደረገችው ሴተኛ አዳሪነትን እንደነበር የነገረችን ሰሎሜ ሙሴም ታሪኳን እንዲህ አውግታናለች፡፡
ብዙ ችግር እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የነበሩት እነዚኽ እናቶች፥ ገባሬ ሠናይ ድርጅቱን የሚገልጹት፣ ሕልማቸውን የሚያሳኩበት እና ሕይወታቸውን የሚቀይሩበት ዕድል እንደፈጠረላቸው ነው፡፡
ነፃ የሕፃናት መቆያ፣ ነፃ ትምህርት፣ ነፃ ምግብ፣ እንዲሁም ነፃ የሕክምና አገልግሎት ለሕፃናቱ የሚሰጠው የ“ግሬስ” ማዕከል፣ ከሦስት ዓመት ተኩል በላይ የኾኑ ሕፃናትን፣ ከማዕከሉ ውጭ ኾነው እንዲያድጉ፥ ሞግዚት በመቅጠር ያመቻቻል፡፡ ወላጅ ላላቸው እና ችግረኛ ለኾኑ ሕፃናት፣ ወላጆቹ የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ ሰጥቶ ከልጆቻቸው ጋራ እንዳይለያዩ ያደርጋል፡፡ ከእነዚኽ ውስጥ አንዱ፣ አቶ መንግሥቱ ማንደፍሮ ነው፡፡
የችግረኛ ሕፃናትንና የወላጆችን የሕይወት መሥመር እየቀየረ ያለው ይህ ማዕከል፣ በዋናነት በአሜሪካዊቷ ሜርሲ ሜሪክሰን ቢንቀሳቀስም፣ በሥሩ ሌሎች በጎ አድራጊ ግለሰቦች እንዳሉ፣ አቶ ወርቁ ይናገራል፡፡
የዐማራ ክልል የሴቶች እና ሕፃናት ቢሮ፣ የሕፃናት መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዴ፣ ስለ ማዕከሉ ባላቸው ምዘና፣ “ግሬስ” ማዕከል፣ ለሕፃናት እና ለሴቶች የሚያደርገው ድጋፍ፣ ችግር ፈቺ ስለመኾኑ ቢሮው ተምሮበታል፡፡ በሌሎች የክልሉ ዋና ዋና ከተሞችም፣ ተመሳሳይ ማዕከሎችን ለመክፈት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ወርቁ እንደሚሉት፣ ሕፃናቱ፣ ለመኖር መሠረታዊ የኾኑ ፍላጎቶችን እንደ አስፈላጊነቱ ከሚሰጡ የሥነ ልቡና የምክር አገልግሎት ጋራ፣ በዚኽ ማዕከል ያገኛሉ፡፡ ይህም ኾኖ፣ ሰብአዊ ፍቅር ሰጥቶ የሚያሳድጋቸው፣ ቤተሰብም ማኅበረሰብም ያስፈልጋቸዋል፡፡
በአንድ ማዕከል ውስጥ ሕፃናትን ሰብስቦ ማሳደግ፣ ጊዜአዊ የችግር መፍቻ መፍትሔ ሊኾን ይችላል፡፡ ነገ የሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት፣ ዛሬ በሕፃናቱ ላይ መልካም ዘር መዝራት ያስፈልጋል፡፡ ዘሩ የሚዘራው ደግሞ፣ አንድም በቤተሰብ፣ ኹለትም በማኅበረሰብ ነው፡፡ ለዚኽ ደግሞ፣ ማኅበረሰቡ ሕፃናቱን ወስዶ በማሳደግ አልያም ደግሞ በየጊዜው መጥቶ በመጎብኘት ፍቅር እንዲሰጥ፣ የማዕከሉ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቁ ሐሳብ፣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡