የሲዳማ ክልል 136 አመራሮችን በሙስና ከሠሠ

Your browser doesn’t support HTML5

የሲዳማ ክልል 136 አመራሮችን በሙስና ከሠሠ

የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የክልሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር እና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ሓላፊዎችን ጨምሮ 136 አመራሮች እና ባለሞያዎች፣ በሙስና ወንጀል መከሠሣቸውን አስታወቀ።

ክሥ ከተመሠረተባቸው መካከል 72ቱ፣ ከአንድ እስከ 11 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ገልጿል።

በሙስና እና ብልሹ አሠራር በሕግ እንዲጠየቁ የተለዩት 505 አመራሮች እና ባለሞያዎች ሲኾኑ፣ መዝብረዋል የተባሉትን 60 ሚሊዮን ብር ተመላሽ ማድረጉን፣ የሲዳማ ክልል ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ማቶ ማሩ አስታውቀዋል።

የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ማቶ ማሩ፣ ትላንት ሰኞ፣ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የሌብነት እና ምዝበራ ወንጀል የተፈጸመው፥ ለኢንቨስትመንት በሚል መሬት በመቀራመት፣ የፋይናንስ ሥርዐቱን በመጣስ፣ በመንግሥት ቤቶች አስተዳደር፣ በገቢ ግብር እና ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን በማዘጋጀት እንደኾነ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አብራርተዋል፡፡

በሙስና ወንጀል እና በብልሹ አሠራር ለተጠየቁ ሁለት ደንበኞቻቸው ጥብቅና መቆማቸውን የተናገሩት አቶ ዓለማየሁ አየለ፣ አንዱ ደንበኛቸው ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ ገልጸው፤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ለተፈረደበት ሌላ ደንበኛቸው ይግባኝ መጠየቃቸውን ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ተናግረዋል።

የቁጥጥር እና ክትትል ሥራው፣ በክልሉ መንግሥት በተቋቋመው ኮሚቴ መከናወኑን የተናገሩት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ማቶ ማሩ፣ በሒደቱ፣ ከሕዝብ 118 ጥቆማዎች መቀበላቸውንና የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

ከኅብረተሰቡ የተሰጡ ጥቆማዎች በምርመራ መለየታቸውን የጠቀሱት የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ መሬትን ጨምሮ የተመዘበረ የሕዝብ ሀብትን ለማስመለስ በተደረገ ጥረት ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በሐዋሳ፣ በይርጋለም፣ በለኩ እና ሆኮ ከተሞች፣ በሕገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች ተላልፎ የነበረ ከአምስት ሄክታር በላይ መሬት፣ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል፤ ብለዋል።

በሲዳማ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አንዳንዶቹ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሚያወጧቸው መግለጫዎች፣ በክልሉ፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራር ተንሰራፍቷል፤ ሲሉ፣ በገዥው ፓርቲ እና በመንግሥት ላይ ወቀሳ እና ትችት ያቀርባሉ።

የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ማቶ፣ መረጃ እና ማስረጃ ቀርቦበት፣ በሕግ የማይጠየቅ አካል እንደማይኖር አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በ193 መዝገቦች ክሣቸው እየታየ የሚገኙት የቀሪዎቹ 369 አመራሮች እና ባለሞያዎችም ጉዳይ፣ በፍርድ ሒደት ላይ መኾኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፣ በሙስና እና ብልሹ አሠራር የተሳተፉ ባለሥልጣናትን በሕግ የመጠየቁ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።