የሠላም ስምምነቱን 6ኛ ወር ምክንያት በማድረግ አንተኒ ብሊንከን መግለጫ ሰጡ

በኢትዮጵያ መንግስትና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሠላም ሥምምነት ስድስተኛ ወር ምክንያት በማድረግ አንተኒ ብሊንከን ትናንት ባወጡት መግለጫ ለሥምምነቱ ተግባራዊነት ሁለቱ ወገኖች ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።

ስምምነቱ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች መልሰው እንዲሰጡ፣ የዕርዳታ ፍሰት እንዲቀጥል፣ ሕወሓት ከባድ መሣሪያዎችን እንዲያስረክብ፣ የታገቱ ሰዎች እንዲለቀቁ፣ ሁሉን አቀፍና ሁሉን አካታች የሽግግር ፍትህ ሃሳብ እንዲንቀሳቀስ፣ እንዲሁም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቁቋም አስችሏል ብለዋል ብሊንከን በመግለጫቸው።

“በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የተካሄደውና ዩናይትድ ስቴትስ በታዛቢነት የተሳተፈችበት ሥምምነት ፍሬያማ መሆን በአህጉሪቱ ‘ጠመንጃን ጸጥ ማሰኘት’ ለተሰኘውና በኅብረቱ ለሚካሄደው ዘመቻ በአርዓያነት የሚታይ እንዲሁም የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት እየሰጡ ላሉት መልካም አመራርና የኅብረቱ ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጥረትን ፍሬያማነት የሚያሳይ ነው” ብለዋል አንተኒ ብሊንከን ባወጡት የጽሁፍ መግለጫ።

ብሊንከን በማያያዝ አገራቸው የሰላም ስምምነቱ ትግበራ እንዲቀጥል የምታበረታታ መሆኑንና፣ ይህም ሲቪሎችን ለመከላከል ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ሥርዐት እንዲኖር፣ ውጤታማ የሆነ ትጥቅ ማስፈታትና የሠራዊት ብተና እና ወደ ማሕበረሰቡ መልሶ ማቋቋም የመሳሰሉት እንዲከናወኑ የምታበረታታና የምትከታተል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኤርትራ እና ከፌዴራል ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ተጠያቂ መደረጋቸውን የሚጨምር ተአማኒነት ያለው የሽግግር ፍትህ መኖር በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ቆልፍ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል ብሊንከን፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ውጤታማ የሰላም ሂደት መኖር በኦሮሚያ ክልል ሠላምን ለማምጣት መልካም አጋጣማን ያመጣል ያልት ብሊንከን፣ በታንዛኒያ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የሚደረገውን ንግግር በመልካም እንደምትቀበለውና ሁለቱ ወገኖች በቅን ልቦና እንዲደራደሩ እናበረታታለን ብለዋል፡፡

በተጠቀሱትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የመሥራቱን አስፈላጊነት ትገነዘባለች፣ ለዚህም ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ታረጋግጣልች ሲሉ ብሊንከን መግለጫቸውን ደምድመዋል፡፡